አርዕስተ ዜና

የደቡብ ሱዳን ጁባ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ ታገደ

267 times

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2010 በደቡብ ሱዳን ርዕሰ መዲና ጁባ የሚገኘው የጁባ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ ታገደ።

ስታዲየሙ የታገደው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ መስፈርቶችን ባለማሟላቱ እንደሆነ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) አስታውቋል።

አንድ ስታዲየም ዓለም ዓቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ከ20ሺህ በላይ ሰዎችን የመያዝ አቅም፣ ተጓዳኝ የሆኑ የስፖርት ውድድሮችን የሚያካሂድ፣ የመገናኛ ብዙሀን መዘገቢያ ቦታ (media room) ያለው፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የሜዳው ምቹነትና ስታዲየሙ ደረጃውን ጠብቆ እንዲቆይ ተከታታይነት ያለው ጥገና ወይም ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በተጨማሪም ስታዲየሙ በከፊልም ቢሆን ጣሪያ ያለው፣ በአብዛኛው የመቀመጫ ወንበሮች የተሟሉለት፣ የአምቡላንስ መኪኖች መተላለፊያ መንገድ የተሰራለትና የመጫወቻ ሜዳውም የተፈጥሮ አሊያም ሰው ሰራሽ ሳር የለበሰ ሊሆን ይገባል።

እ.አ.አ በ1962 ስራ የጀመረውና ሰባት ሺህ ደጋፊዎችን የሚያስተናግደው የጁባ ስታዲየም ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች ባለማሟላቱ ዓለም ዓቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ ታግዷል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እ.አ.አ በ2012 ስታዲየሙ በጊዜ ሂደት መስፈርቶችን ያሟላል በሚል ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት እንዲያስተናግድ ፈቅደው ነበር።

ይሁን እንጂ ስታዲየሙ ምንም አይነት ማሻሻያ ያልተደረገለት በመሆኑ ከዚህ በኋላ የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድንና የአገሪቷ ክለቦች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጨዋታዎችን በኡጋንዳና በሱዳን ስታዲየሞች እንደሚያደርጉ ካፍ አስታውቋል።

  

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን