አርዕስተ ዜና

18 የክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት አሰልጣኞች የ2ኛ ደረጃ አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አገኙ

248 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 በበጀት አመቱ  በሶስት ዙር በተሰጡ የሙያና ደረጃ ማሻሻያ ስልጠናዎች 18 የክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት አሰልጣኞች የ2ኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አገኙ።

የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀቱን ካገኙት መካከል 15ቱ ወንዶች ሲሆኑ ሶስቱ ሴቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ አሽኔ ለኢዜአ እንደገለጹት የምስክር ወረቀቱን ያገኙት በታዳጊ ፕሮጀክትና በግላቸው የሚያሰለጥኑ ናቸው።

በአዳማ ከተማ የተሰጡት እነዚህ ስልጠናዎች ፌዴሬሽኑና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በትብብር ያዘጋጇቸው መሆናቸውን የጽህፈት ቤት ሃላፊው ተናግረዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ፈተናዎችን በብቃት በማለፍ የአሰልጣኝነት ደረጃቸውን ከፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የሁለተኛ ደረጃ አሰልጣኞቹ የክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመክፈት ስፖርተኞችን ማስተማር እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በዚህም በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ የተሻሉ ስፖርተኞችን በማፍራት ለስፖርቱ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ስልጠናው በክልሎች ያለውን የአሰልጣኞች እጥረት በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ያግዛልም ብለዋል።

አንድ ሴትና አንድ ወንድ አሰልጣኝ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም በኬንያ በተካሄደ የክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት አሰልጣኞች የልምድ ልውውጥ ላይ መሳተፋቸውን አቶ አበበ አክለዋል።

ከአሰልጣኞች የደረጃ ማሳደግ በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት በአዳማ በተሰጠ የዳኝነት ስልጠና 11 ወንድና ሶስት ሴት የክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት ዳኞች የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ነው ያብራሩት።

ከስልጠናው በተጨማሪ ስፖርቱን ለማሳደግና ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ በየክልሉ የግንዛቤ ማስጨበጥና የቅስቀሳ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ፌዴሬሽኑ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተያዘው የሚያዝያ ወር የክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት የአሰልጣኝነት ትልቁ ደረጃ የሆነውን የሶስተኛ (ኢንስትራክተርነት) ደረጃ  ስልጠና ለመስጠት እቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌደሬሽን በተያዘው በጀት ዓመት ለ130  አሰልጣኞች የመጀመሪያ ደረጃ  ለ35 ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና ሰጥቷል። በተጨማሪም 13 ዳኞች የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና አግኝተዋል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን