አርዕስተ ዜና

አትሌት አብደላ ጎዳና የጃፓን ናጋኖ ማራቶንን አሸነፈ

191 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2010 ኢትዮጵያዊው አትሌት አብደላ ጎዳና የጃፓን ናጋኖ ማራቶን ውድድርን አሸነፈ።

አትሌቱ ዛሬ ማለዳ በተካሄደው ውድድር ሁለት ሠዓት ከ13 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ በመግባት ነው ያሸነፈው።

ጃፓናዊው ዩኪ ሙናካታ በሁለት ሠዓት ከ14 ደቂቃ ከ21 ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል።

ሁለት ሠዓት ከ14 ደቂቃ ከ42 ሴኮንድ በመግባት ሶስተኛ የወጣው ጃፓናዊ ሂሮሺ ኢቺዳ የርቀቱን የግል ምርጥ ሠዓት አስመዝግቧል።

በዚህ ውድድር ከ2ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ጃፓናዊያን አትሌቶች ናቸው።

በሴቶች ውድድርም ጃፓናዊያኖቹ አትሌቶች አሳሚ ፉሩስ፣ ሳኪ ቶኮሮ እና ዩኪኮ ኦኩኖ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በበላይነት አጠናቀዋል።

ኬንያዊቷ ፖል ዋንጉዊ አራተኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቃለች።

ለ20ኛ ጊዜ የተካሄደው የናንጋኖ ማራቶን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

በሌላ ዜና ዛሬ በአሜሪካው የቦስተን ማራቶንና በፓላንድ የሎድዝ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ዛሬ ከሌሊቱ በስድስት ሠዓት በሚካሄደው የቦስተን ማራቶን በወንዶች ሌሊሳ ደሲሳ፣ ለሚ ብርሃኑና ታምራት ቶላ ይወዳደራሉ።

በሴቶች ውድድርም አትሌት አሰለፈች መርጊያ ትሳተፋለች።

በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኤርትራ አትሌቶች የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ማግኘታቸውን ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።

በሁለቱም ጾታዎች ከአንደኛ እስከ 12ኛ ለሚወጡ አትሌቶች በአጠቃላይ የ706 ሺህ ዶላር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን አንደኛ የሚወጡ አትሌቶች 150 ሺህ ዶላር እንደሚሸለሙ የቦስተን አትሌቲክስ ማህበር አስታውቋል።

በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የቦስተን ማራቶን ለ122ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።

በተመሳሳይ በፓላንድ የሎድዝ ማራቶን አትሌቶቹ መስፍን አለሙ፣ አንዱአለም በላይ፣ አስማረ ወርቅነህና ታረቀኝ ዘውዱ ይሳተፋሉ።

በሴቶች አትሌት መሰረት መርኔና አትሌት ለምለም በርኸ ይካፈላሉ።

 

Last modified on Monday, 16 April 2018 18:23
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን