አርዕስተ ዜና

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታ ኮንጎ ብራዛቪል ገብቷል

197 times

 አዲስ አበባ  መጋቢት 7/2010 ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከአትሌቲክ ሬኔሳንስ አይግሎን ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ኮንጎ ብራዛቪል ገባ።

 ቅዱስ ጊዮርጊስና አትሌቲክ ሬኔሳንስ አይግሎን የፊታችን ረቡዕ 33 ሺህ ደጋፊ በሚያስተናግደው በስታድ አልፖንስ ማሴምባ-ዴባት ስታዲየም ከቀኑ በ10 ሠዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

 የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምኒልክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት 18 ተጫዋቾችና ዘጠኝ የልዑካን ቡድን አባላትን ይዞ ዛሬ ማለዳ የተጓዘው ክለቡ ኮንጎ ብራዛቪል ገብቷል።

 ቡድኑ ብራዛቪል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የአገሪቷ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካዮች አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን የመገናኛ ብዙሃንም የልዑካን ቡድኑን መድረስ ለመዘገብ ተገኝተዋል።

 የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የመጀመሪያውን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ለመልሱ ጨዋታ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ምኒልክ ገልጸዋል።

 የመጨረሻ ልምምዳቸውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃቸውንም አክለዋል።

 በመጀመሪያው ጨዋታ በጉዳት ያልተሰለፈው የመሐል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ በቡድኑ ተካቶ ወደ ብራዛቪል አቅንቷል።

 ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳነ ግርማ ጎል አንድ ለዜሮ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይ በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ቡድን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ድልድሉ ይገባል።

 በተመሳሳይ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ የፊታችን ረቡዕ ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ በአስር ሠዓት ይጫወታል።

 የክለቡ ቡድን መሪ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ከወላይታ ድቻ ጋር ጨዋታውን የሚያደርገው ያንግ አፍሪካንስ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባቱንና ከሠዓታት በኋላም ሃዋሳ እንደሚደርስ ገልጸዋል።

 ጨዋታውን የሚመሩት የኡጋንዳ ዳኞች እንዲሁም ጅቡቲያዊው የጨዋታው ኮሚሽነር ነገ አዲስ አበባ ገብተው ቀጥታ ወደ ሃዋሳ እንደሚጓዙ ጠቁመዋል።

 ወላይታ ድቻ ያለፈውን ጨዋታ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ካደረገ በኋላ ለመልሱ ጨዋታ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል።

 ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝና የመጀመሪያውን ጨዋታ ውጤት በመቀልበስ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።

 ከሳምንት በፊት በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያንግ አፍሪካንስ ሁለት ለዜሮ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

 ወላይታ ድቻ የግብጹን ዛማሌክን በሜዳው አሸንፎ ወደ 32 ውስጥ በመግባት በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ታሪክ ማስመዝገቡ አይዘነጋም።

Last modified on Sunday, 15 April 2018 22:43
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን