አርዕስተ ዜና

በፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ አገራት ጨዋታቸውን ነገ ያካሂዳሉ

11 Jan 2018
368 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2010 የ2018 የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ ብሔራዊ ቡድኖች የሚለዩበት የማጣሪያ ጨዋታዎች ነገ ይጀምራሉ።

ለዘጠነኛ ጊዜ በፈረንሳይ ለሚካሄደው ለዚህ ውድድር በተለያዩ አህጉራት የማጣሪያ ጨዋታዎች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ፤ አፍሪካም በሁለት አገራት እንድትወክል ኮታ ተሰጥቷታል።

በዚህም መሰረት በውድድሩ ለመሳተፍ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ነገ መካሄድ ይጀምራሉ።

የደቡብ አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው እንዲሁም የካሜሮን ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከጋና አቻው ጋር ጨዋታቸውን ነገ ያደርጋሉ።

የመልስ ጨዋታዎች ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም የሚያከናውኑ ሲሆን፤ በደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሆኑ ሁለት አገራት አፍሪካን ወክለው በውድድሩ ይሳተፋሉ።

የደቡብ አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የናምቢያ፣ የብሩንዲ እንዲሁም ናይጄሪያ፣ የሞሮኮንና የታንዛንያ አቻቸውን በደርሶ መልስ ጨዋታ በማሸነፍ ለመጨረሻው ዙር ማጣሪያ መድረሳቸው ይታወቃል።

የጋና ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ አልጄሪያና ኬንያን በማሸነፍ ለመጨረሻው ማጣሪያ መድረስ ችሏል።

በአንጻሩ የካሜሮን አቻው ከጊኒና ከሴራሊዮን ጋር እንዲጫወት መርሀ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ራሳቸውን በማግለላቸው ያለ ምንም ጨዋታ ለመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ለመሳተፍ የማጣሪያ ውድድር በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም ከኬንያ አቻው ጋር ጨዋታውን አድርጎ በደርሶ መልስ አራት ለሶስት በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከመጀመሪያው ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

ቻይና፣ጃፓን፣ሰሜን ኮሪያ፣ኒውዝላንድ፣ፈረንሳይ፣እንግሊዝ፣ጀርመን፣ስፔንና ኔዘርላንድ በውድድሩ ላይ መሳታፋቸውን ያረጋገጡ አገራት ሲሆኑ ፈረንሳይ አዘጋጅ በመሆኗ በቀጥታ በውድድሩ ላይ ትሳተፋለች።

በተያዘው ጥር ወር በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ እንዲሁም በሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካና ካሪቢያን አገራት የሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ ቀሪ ሰባት አገራትን የሚለዩ ይሆናል።

16 ቡድኖች የሚሳተፉበት ዘጠነኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል።

ጀርመንና አሜሪካ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ የውድድሩ ሻምፒዮን ሲሆኑ ሰሜን ኮሪያ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችላለች።

ፈረንሳይ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ በተጨማሪ ስምንተኛውን የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ ሰኔ 2011 ዓ.ም ታሰተናግዳለች።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ