አርዕስተ ዜና

የ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይጀምራሉ

11 Jan 2018
297 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2010 11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበበና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

በወጣው መርሀ ግብር መሰረት የዚህ ሳምንት ጨዋታዎች አርብ፣ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እንደሚከናወኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታወቋል።

ነገ ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከመቀለ ከተማ ከቀኑ አስር ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለፈው ሳምንት የቦታ ለውጥ ካደረገባቸው ሶስት ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው።

እሁድ ደደቢት ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ አስር ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞች ጅማ አባ ጅፋር ከመከላከያ፣በደቡብ ደርቢ ወላይታ ድቻ ከአርባ ምንጭ ከተማ፣አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ሐዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌትሪክ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት የሚጫወቱ ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት 30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፕሪሚየር ሊጉን ደደቢት በ22 ነጥብ ሲመራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16 ነጥብ ሁለተኛ፣ ፋሲል ከተማና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 15 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ሲይዙ  ጅማ አባ ጅፋርና መቀለ ከተማ በተመሳሳይ በ14 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሀዋሳ ከተማና ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሰባተኛና ስምንተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ድሬዳዋ ከተማ፣ኢትዮ-ኤሌትሪክና አርባ ምንጭ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16 ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኮከብ አግቢነቱን የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና ጋናዊው የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተጫዋች አል ሀሰን ካሉሻ በተመሳሳይ በሰባት ጎል ሲመሩ፣  ናይጄሪያዊው የጅማ አባ ጅፋር ተጨዋች ኦኪኪ አፎላቢ በስድስት ጎል፣የደደቢቱ አቤል ያለውና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ በአምስት ጎሎች ይከተላሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ