አርዕስተ ዜና

አትሌት ሐይሌ ቶሎሳ በማንኛውም ስፖርት እንዳይሳተፍ ታገደ

10 Jan 2018
349 times

አዲስ አበባ ጥር 2/2010 ኢትዮጵያዊው አትሌት ሐይሌ ቶሎሳ በ2008 ፔሩ ላይ በተካሄደው ማራቶን ላይ አበረታች መድሐኒት በመጠቀሙ የአራት ዓመት ቅጣት ተላለፈበት።

የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይ ደብል ኤፍ)  አትሌቱ በውድድሩ ላይ "ቤንዞይሌክጎናይን" እና "ሜቲሌክጎናይን" የተባሉ የኮኬን ንጥረ ነገር ያላቸውን ቅመሞች መጠቀሙን በማረጋገጡ ነው ቅጣቱ የተላለፈበት።

ቅመሞቹ በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች መድሃኒት ኤጄንሲ ባስቀመጠው የተከለከሉ ንጥረ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ በመሆናቸው ነው አትሌቱ ላይ እርምጃ የተወሰደው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤትም ማህበሩ የላከውን መረጃና የውሳኔ ሀሳብ መነሻ በማድረግ ውሳኔ ማሳለፉን ለኢዜ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

አትሌት ሐይሌ ቶሎሳ የህግ ጥሰቱን የማጣራት ሂደት ከተጀመረበት ሚያዝያ 2008  ጀምሮ ታሳቢ በማድረግ እስከ ግንቦት 2012  ድረስ ለአራት ዓመታት በማንኛውም አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፍ ቅጣት ተላልፎበታል።

ጽህፈት ቤቱ በቀጣይም አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የፀረ-አብረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ በተለይም የህግ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁሟል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በውድድር ጊዜና ከውድድር ውጭ የስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ በማካሄድ ላይ መሆኑንና በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣ በብስክሌት፣ በቦክስና በፓራ ኦሎምፒክ ስፖርቶች ከ624 በላይ የሽንትና የደም ምርመራ ማድርጉን አስታውቋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካልም ከጸረ አበረታች ነጻ የሆነ ስፖርት በማስፋፋት በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው የሚያሸንፉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

የስፖርት አበረታች መድሃኒቶችን በመጠቀም ያልተገባ ውጤት የማስመዝገብ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገራችን ስፖርት በተለይም የአትሌቲክሱ ስጋት እየሆነ መጥቷል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 ራሱን ችሎ መቋቋሙ በመግለጫው ተጠቅሷል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ