አርዕስተ ዜና

ወጣቶች ከስሜታዊነት ተቆጥበው ለስፖርቱ ማደግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

10 Jan 2018
253 times

ደብረ ብርሃን ጥር 2/2010 ስፖርታዊ ውድድሮች የእርስ በርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ የመዝናኛ ፋይዳቸው እንዲጎላ ወጣቶች ከስሜታዊነት ተቆጥበው ለስፖርቱ ማደግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን አንድ ሺህ 500 ስፖርተኞች የተሳተፉበት ዞን አቀፍ የስፖርት ውድድር በአጾኪያ ገምዛ ወረዳ መኮይ ከተማ ትናንት ተጀምሯል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ በመክፈቻ ላይ እንደገለጹት ስፖርት የፍቅር፣ የመቻቻልና በውድድር የአሸናፊነት ብቃት ማሳያ መሆን አለበት።

" ከመዝናኛ ፋይዳው ባለፈ ለሰላም፣ ለልማትና ለእርስ በእርስ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠሪያ መድረክ ሆኖ ማገልገልም ይኖርበታል" ብለዋል።

በመሆኑም ሰላማዊ የስፖርት ውድድር እንዲካሄድ ወጣቶች ከስሜታዊነት ተቆጥበው ለስፖርቱ ማደግ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከላይ ሳህለማሪያም በበኩላቸው "ውድድሩ በወልዲያ ከተማ ለሚካሄደው የመላው አማራ ስፖርት ወድድር ተሳተፊ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ለመምረጥ የሚያስችል ነው" ብለዋል።

በውድድሩ የብስክሌት፣ የመረብ ኳስ፣ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስን ጨምሮ 17 ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆን በእዚህም አንድ ሺህ 500 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የአጾኪያ ገምዛ ወረዳ ሕዝብና ባሳዑዲ አረቢያ ጅዳ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ባዋጡት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ያስገነቡት የስፖርት ማዘውተሪ ቦታ ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ ሆኖ እንደሚታይ አቶ ከላይ አመልክተዋል።

ከበረኸት ወረዳ ተሳታፊ ስፖርተኛ ወጣት ታምር በለጠ እንዳለው ስፖርት ለጤንነት፣ ለወዳጅነት፣ ለልማትና ለመልካም ግንኙነት ከሚኖረው ጥቅም ባለፈ የወረዳዎችን ባህልና እሴት ለማወቅ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

የመኮይ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘሩ አካሉ በበኩላቸው ውድድሩ በስፖርታዊ ቱሪዝም የአካባቢው ነጋዴዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከማገዝ ጀምሮ ለወጣቶቹ አካባቢውን በማስተዋወቅ በኩል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ በተካሄደ የእግር ኳስ ውድድር አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ኤፍራታና ግድም ወረዳን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በውድድሩ መክፈቻ ላይም ከ22 የገጠር ወረዳዎችና ከሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የልኡካን ቡድኖች የመጡበትን አካባቢ ባህልና ወግ ለታዳሚው አሳይተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ