አርዕስተ ዜና

የ2017 የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ምርጫ ነገ ይካሄዳል

03 Jan 2018
395 times

አዲስ አበባ  ታህሳስ  25/2010  የ2017 የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ነገ በጋና ርዕሰ መዲና አክራ ይካሄዳል።

 በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊ የሚሆኑት ተጫዋቾች፣ ብሔራዊ ቡድኖች፣ ክለቦችና አሰልጣኞች በአክራ ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ማዕከል በሚካሄደው ስነ ስርአት እንደሚለዩ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) በድረ ገጹ አስፍሯል።

 የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት መስጠት በተጀመረበት እ.አ.አ በ1992 የመጀመሪያው አሸናፊ የነበረው ጋናዊው አብዲ ፔሌን ጨምሮ እስከ ባለፈው ዓመት ኮከብ ተጫዋች አልጄሪያዊው የሌይስተር ሲቲ ተጫዋች ሪያድ ማህሬዝ በሽልማት ስነ ስርአቱ ይታደማሉ።

 በስነ ስርአቱ ላይ የናይጄሪያ የቀድሞ ታዋቂ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ኢማኑኤል አሞኒኬ፣ንዋንኮ ካኑና ቪክቶር ኢክፔባ እንዲሁም አራት ጊዜ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች የሆኑት በቅደም ተከተል ካሜሮናዊውና ኮትቫራዊው ሳሙኤል ኢቶና ዲዲየር ድሮግባ ይገኛሉ። 

 ካሜሮናዊው የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፓትሪክ ሞምቦባ፣ኮትቫራዊው ያያ ቱሬ፣ሴኔጋላዊው አል ሀጂ ዲዩፍ፣ሞሮካዊው ሙስጠፋ ሀጂና ቶጎአዊው ኢማኑኤል አዲባየር በሽልማት ስነ ስርአቱ ላይ የሚገኙ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው።

 በተጨማሪም ከዚህ በፊት በሴቶች ዘርፍ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋቾችና ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተጫዋቾችና አመራሮች እንደሚገኙም ካፍ ገልጿል።

 በዚህም መሰረት በወንዶች ግብጻዊው መሐመድ ሳላህና የሴኔጋሉ ሳዲዮ ማኔ ከእንግሊዙ የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ እንዲሁም ጋቦናዊው ፒዬር ኤሜሪክ ኦቦሚያንግ ከጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትሙንድ ክለብ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሆነው ተመርጠዋል።

 በሴቶች ናይጄሪዊቷ አሲሳት ኦሾአላ ከቻይናው ዳሊያን ኩዋንጂያን፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ ክርስቲና ጋትላና በአገሯ ሊግ ከሚገኘው ዩ.ደብሊው.ሲ ሌዲስ ክለብና የሩሲያው ሲ.ኤስ.ኤ ሞስኮ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቿ ካሜሮናዊት ጋብሪኤሌ አቡዲ ኦንግዌኔ የመጨረሻው ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።

 ሴኔጋላዊው ክሬፒኒ ዲያታ ከኖርዌዩ ሳርስፖርግ ክለብ፣ ዛምቢያዊው ፓትሰን ዳካ ከኦስትሪያው ሊፈሪንግ ክለብና ለማሊው ጉዊዳራ ክለብ የሚጫወተው ማሊያዊው ሳላም ጊዱ የአፍሪካ ወጣቶች የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች የመጨረሻ ሶስት እጩዎች ውስጥ መካተት ችለዋል።

 የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ አሰልጣኞች እጩዎች የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጀርመናዊው ግሬኖት ሮር፣ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስፔናዊው ሄክቶር ኩፐርና ሞሮኳዊ ዜግነት ያላቸው የአገሪቷ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ አሰልጣኝ ሁሴን አሙታ ናቸው።

 የግብጹ አልአሀሊ፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤና የሞሮኮው ዋይዳድ አትሌቲክ ክለቦች ደግሞ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ክለብ ለመባል በእጩነት ተመርጠዋል።

 ካሜሮን፣ ግብጽና ናይጄሪያ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ዝርዝር ውስጥ የገቡ ሲሆን በሴቶች የጋናና የናይጄሪያ  ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንና የደቡብ አፍሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ምርጥ የሴት ብሔራዊ ቡድን ሆኖ ለመመረጥ ይፎካከራሉ።

 ማዳጋስካራዊው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ የሽልማቱን ስነ ስርአት አስመልክቶ በአክራ ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ማዕከል ዛሬ ከሰአት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ የካፍ ዘገባ ያመላክታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ