አርዕስተ ዜና

አረጋውያንን መደገፍ አላማ ያደረገ የጎዳና ላይ ሩጫ በድሬዳዋ ተካሄደ

01 Jan 2018
397 times

ድሬዳዋ ታህሳስ 23/2010 አረጋውያንን ለመደገፍና ለመንከባከብ ዓላማ ያደረገ የ5ሺህ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በድሬዳዋ ተካሄደ ፡፡

"እኔም ለአረጋውያን እሮጣለሁ" በሚል መርህ ትላንት በተካሄደው የጎዳና ላይ ውድድር ከ10ሺህ በላይ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ህጻናቶች፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎች፣ አዛውንቶች፣ አርቲስቶችና አትሌቶች በሩጫው ተሳትፈዋል።

˝በዳዊት ለአረጋውያን የበጎ አድራጎት ማህበር˝ የተዘጋጀውን የጎዳና ሩጫ ያስጀመሩት የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ናቸው፡፡

ከንቲባ ኢብራሂም በወቅቱ እንደተናገሩት አረጋውያን ባላቸው ልምድ በሀገር ልማትና ዕድገት ውስጥ ተሣትፎአቸውን እንዲያጠናክሩና ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ አስተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል ።

"ማህበሩ እየተካሄደ ላለው የአረጋውያን ድጋፍና እንክበካቤ ማእከል ግንባታ አስተዳደሩ 5ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቷል " ብለዋል ።

የበጎ አድራጎት ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት በቀለ በሩጫው የተሳተፉ ነዋሪዎችን አመስግነው ከሩጫው የተገኘው ገቢ ማህበሩ እያስገነባ ላለው የአረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ ማእከል ግንባታ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል ።

እየተካሄደ ላለው የማእከሉ ግንባታ 52ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ ዳዊት "ግንባታው ከተያዘለት የአምስት አመት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው "ብለዋል ።

አስተዳደሩ፣ነዋሪው፣ ባለሀብቱና አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ።

የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ውድድርና ተሳትፎ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብዶ ሙሜ በበኩላቸው ማህበሩ ለአረጋውያን ድጋፍ የሚውል ስፖርታዊ ውድድሮችን  በማዘጋጀትና ገቢ ለማሰባሰብ በሚያደርገው ጥረት ሁሉ የኮሚሽኑ ድጋፍ እንደማይለየው ተናግረዋል ።

ኮሚሽኑ ለሩጫው መሳካት ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፍ ማድረጉን አቶ አብዶ አስታውቀዋል።

በሩጫው የተሳተፉ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው ነዋሪዎች አረጋውያንን ለመደገፍና ለመርዳት በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ