አርዕስተ ዜና

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለዜሮ አሸነፈ

31 Dec 2017
398 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2010 ዛሬ በዘጠነኛ ሳምንት በተደረገ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለዜሮ አሸነፈ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው የሳምንቱ ተጠባቂ የሊጉ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ደደቢት በጌታነህ ከበደ ባስቆጠረው ግብ ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፍ ችሏል።

የደደቢቱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ በሊጉ ያስቆጠረውን ግብ ወደ አምስት አሳድጎታል። የዛሬው ውጤት ክለቡ በሊጉ ያለውን ነጥብ ወደ 19 በማሳደግ መሪነቱን እንዲያጠናክር አድርጎታል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም የደደቢቱ ጋናዊ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ አድኗቸዋል።

በተመሳሳይ ዛሬ በክልል ጨዋታዎች ተካሂደዋል። ሀዋሳ ከተማ ከመቀለ ከተማ ባደረገው ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተለያይተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አዳማ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ትናንት በተካሄዱት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተለያይቷል። ድሬድዋ ከተማ ከፋሲል ከተማ ባደረጉት ጨዋታ አንድ ለአንድ ተለያይተዋል።

ጅማ አባጅፋር ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ሶስት ለባዶ አሸንፏል።

የዘጠነኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በነገው ዕለት ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፤ ወልድያ ከአርባ  ምንጭ ከተማ ወላይታ ድቻ ከኢትዮ ኤሌትሪክ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፕሪሚየር ሊጉን ደደቢት በ19 ነጥብ ሲመራ፣ ፣ ጅማ አባ ጅፋር በ14 ነጥብ ሁለተኛና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ፋሲል ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ተበላልጠው ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በ12 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኮከብ አግቢነቱን የጅማ አባ ጅፋር ተጨዋች ናይጄሪያዊው  ኦኪኪ አፎላቢና የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተጫዋች ጋናዊው  አል ሀሰን ካሉሻ በተመሳሳይ በስድስት ግብ ሲመሩ፤ የደደቢቶቹ አጥቂዎች አቤል ያለውና ጌታነህ ከበደ በአምስት ግቦች ይከተላሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ