አርዕስተ ዜና

ሁለት ክልሎችና አዲስ አበባ አስተዳደር የቦክስ ስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገላቸው

28 Dec 2017
523 times

 አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2010 የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ለሁለት ክልሎችና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቦክስ ስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

 ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ክልሎችና ለአዲስ አበባ አስተዳደር የተደረገው ድጋፍ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የተገኘ ነው።

 በድጋፍ  የተገኙት  ቁሳቁሶች  የቦክስ መወዳዳሪያ ጫማ፣ ቁምጣ፣ ማሊያ፣ የቦክስ ፎጣ (ጓም)፣ የጥርስ መከላከያና ገምባሌ ናቸው።

 የፌዴሬሽኑ የስፖርት ስልጠናና ውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የተገኙት የስፖርት ቁሳቁሶች  ለታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶችና ለስልጠና ይውላሉ።

 ክልሎቹና የከተማ አስተዳደሩ ታህሳስ 16 እና 17 ቀን 2010 ዓ.ም. የተደረገላቸውን ድጋፍ መቀበላቸውንና የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ ስፖርቱን ወደፊት በማራመድ በኩል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

 እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ በቀጣዩ ሳምንትም ለተቀሩት ሰባት ክልሎችና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የቦክስ ስፖርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረጋል።

 የተከፋፈሉት የስፖርት ቁሳቁሶች በአገሪቷ የቦክስ ስፖርትን ለማሳደግ በተለይም በክልሎች ያለውን አቅም ከማጎልበት አንጻር ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

 ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማሳደግ ከሚያደርገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ የቴክኒክና የክህሎት ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝም ነው አቶ ስንታየሁ ያስረዱት።

 በቀጣይ ለሚደረጉ አህጉርና ዓለም አቀፍ የቦክስ ስፖርት ሻምፒዮናዎች ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሚካሄዱ ውድድሮችን ቁጥር ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

 በአሁኑ ወቅት ስፖርቱ መነቃቃት እየታየበት ያለው የቦክስ ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝና ወደቀድሞ ዝናው እንዲመለስ ፌዴሬሽኑ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

 መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ለስፖርቱ እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

 የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በ1954 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (አይባ) እና የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌደሬሽን አባል ናት።

 የቦክስ ስፖርት በጣሊያን ወረራ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይነገራል።

 

---END---

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ