አርዕስተ ዜና

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይገናኛሉ

07 Dec 2017
1079 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 በስድስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ቅዳሜና እሁድ ቀጥለው ይውላሉ።

ቅዳሜ ህዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን ሌሎች 6 ጨዋታዎች እሁድ ይካሄዳሉ።

ቅዳሜ መከላከያ ከአዋሳ ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጅማ አባ ጅፋር በ9:00 እና በ11:00 ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋሉ።

ጨዋታዎቹ እሁድ ቀጥለው ሲውሉ ድሬዳዋ ከተማ- ከአዳማ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ -ከወላይታ ድቻ፣ መቀሌ ከተማ- ከደደቢት፣ ሲዳማ ቡና- ከወልድያ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ- ከውልዋሎ አዲግራት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።

በተመሳሳይ እሁድ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ በከፍተኛ የፉክክር ስሜት የሚካሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ትልቁ ደርቢ እንደሆነ ይታወቃል።

ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው 36 ጨዋታዎች 20 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 7 ጊዜ ረትቷል፤ በ9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ ትልቁ ግጥሚያ የሆነው የሁለቱ ክለቦች ትንቅንቅ ከ30 እስከ 35 ሺህ ተመልካቾችን በሚያስተናግደው የአዲስ አበባ ስታድዬም እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በ11:30 ሰዓት ይካሄዳል።

ጨዋታው ከወዲሁ በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የሚጠበቅ ሲሆን በስፖርታዊ ጨዋነት የታጀበ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

ፕሪሚየር ሊጉን ውልዋሎ አዲግራት በ9 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲመራ አዳማ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ከሁለት እስከ 4 ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ