አርዕስተ ዜና

ዋሊያዎቹ ነገ በሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ጋር ይጋጠማሉ

04 Dec 2017
903 times

አዲስ አበባ ህዳር 25/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና (ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ) ነገ ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር ይጫወታል።

በምድብ ሁለት የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ነገ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን በካካሜጋ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ያደርጋል።

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ 22 ተጫዋቾችን ይዞ ባለፈው ሳምንት ከኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በምዕራብ በኩል 365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ካካሜጋ አቅንቷል።

ዋልያዎቹ ከህዳር 13 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በውጤት ማጣትና በአቋም መዋዥቅ በስፖርቱ አፍቃሪ ዘንድ አመኔታ ያጣው ቡድኑ ባለፉት 10 ዓመታት ከታዩ ብሔራዊ ቡድኖች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ መሆኑን የመስኩ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

በቅርብ ጊዜ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባደረጋቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤታማ መሆን አልቻለም።  

ብሔራዊ ቡድኑ በህዳር ወር በወጣው የፊፋ የአገራት ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃም 145ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ለአራት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ሻምፒዮን የሆነው እ.አ.አ በ2006 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው ውድድር ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ በሚገኝበት ምድብ ሁለት የሚገኙት ኡጋንዳና ብሩንዲ በማቻኩስ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ባካሄዱት ጨዋታ ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ትናንት በሻምፒዮናው መክፈቻ በምድብ አንድ አዘጋጇ ኬንያ ሩዋንዳን ሁለት ለዜሮ ስታሸንፍ በዛው ምድብ የሚገኙት ሊቢያና ታንዛኒያ ያለ ምንም ግብ ተለያይተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለውድድሩ ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች የ60 ሺህ ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን ትናንት ይፋ አድርጓል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ