አርዕስተ ዜና

ብሔራዊ ቡድኑ የቻን አፍሪካ ዋንጫ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል

11 Nov 2017
1331 times

አዲስ አበባ ህዳር 2/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።

 ጨዋታው በሩዋንዳ  ኪጋሊ ይካሄዳል።

 ብሔራዊ ቡድኑ ሞሮኮ በምታስተናግደው የቻን ውድድር ለመሳተፍ ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ ሶስት ለሁለት በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል።

 ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ለመሳተፍ በሁለት ጎል ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በአንጻሩ ከሜዳዊ ውጭ ያሸነፈው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር የማለፍ ዕድሉን አስፍቷል።

 ቡድኑ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ሁለት ጊዜ መሪ መሆን ቢችልም ውጤቱን ማስጠበቅ ካለመቻሉ ባለፈ የሜዳ ዕድሉንም መጠቀም አልቻለም። 

 የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ግቦች የተቆጠሩት በግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሃኑ ስህተት ነበር።

 የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ አሸናፊ ሞሮኮ በ2018 ለምታስተናግደው የቻን ውድድር ተሳታፊ መሆኑን ያረጋግጣል።

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወንዶች እግር ኳስ ቡድን በሱዳን ተሸንፎ ከ2018ቱ የቻን ውድድር ውጪ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። 

 ሆኖም ግብፅ በአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) በውድድሩ እንድትሳተፍ የቀረበላትን ጥያቄ አለመቀበሏን ተከትሎ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የማጣሪያ ጨዋታ አድርገው አሸናፊው ሞሮኮ በ2018 ለምታስተናግደው የቻን ውድድር እንዲሳተፍ ካፍ ውሳኔ አስተላልፏል።

 የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ 16 አገሮች የሚካፈሉበት ሲሆን የዘንድሮው ውድድር ለ5ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ