አርዕስተ ዜና

የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ሳይቋጭ ተበተኑ

11 Nov 2017
1336 times

አዲስ አበባ ህዳር2/2010 የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ከ45 ቀናት በኋላ በአፋር ክልል እንዲካሄድ የተወሰነው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈጻሚ ምርጫ ጉዳይ ሳይቋጭ ተበተኑ።

 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት አካሂዷል።

 የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በመጀመሪያ ቀን ውሏቸው የፕሬዚዳታዊና የስራ አስፈጻሚ ምርጫው እንዲራዘም ሲወስኑ በ2ኛ ቀን ውሏቸው ደግሞ ምርጫው የሚካሄድበትን ቀንና ቦታ ለመቁረጥና አስመራጭ ኮሚቴ ለማቋቋም ሃሳብ አቅርበዋል።

 ይህም በዋናነት ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን /ፊፋ/ ከሁለት ሳምንት በፊት በላከው ደብዳቤ ምርጫው እንዲራዘም፣  አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞም ፍትሃዊ አሰራር እንዲኖር በማሳሰቡ ነው።

 ይህን መነሻ በማድረግ ክልሎች አንድ ሰው ብቻ በእጩነት እንዲያቀርቡ መደረጉ መተዳደሪያ ደንቡን የሚጥስና ለእግር ኳሱ እድገትም የማይጠቅም ነው ሲሉ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተችተዋል።

 ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ክልሎች የሚያቀርቡት የስራ አስፈጻሚ እጩ አንድ ብቻ እንዲሆን ማድረጉ ስህተት መሆኑን በማመኑና በሌሎች የአካሄድ ችግሮች ምክንያት የምርጫው ቀን እንዲራዘም በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል።

 በጉባኤው መክፈቻ ላይ ፌዴሬሽኑን በቀጣዮቹ አራት ዓመታት በስራ አስፈጻሚነትና በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ ስዎች ምርጫ መቼና የት ይካሄድ የሚለው ውሳኔ በሁለተኛው ቀን ውሎ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

 ከሁሉም በላይ ደግሞ አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም የምርጫውን አካሄድ የሚከተታሉ ሰዎችን የመምረጥ ጉዳይም እንዲሁ።

 በዚሁ መሰረት ምርጫው ከ45 ቀናት በኋላ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንዲካሄድ ተወስኗል።

 ይሁን እንጂ በትልቁ የሚጠበቀው አስመራጭ ኮሚቴ የማቋቋም ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የጉባኤው አባላት ተበትነዋል።

 አማራ ክልልን ወክለው በእጩ ፕሬዚዳንትነት የቀረቡት አቶ ተካ አስፋው አስመራጭ ኮሚቴው የግድ መመረጥ እንደነበረበት ተናግረዋል።

 ገለልተኛ አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምርጫው እንዲካሄድ ካልተደረገ የቀኑ መራዘም አስፈላጊ አልነበረም ሲሉም አክለዋል።

 በሌላ በኩል ደቡብ ክልል በእጩ ፕሬዚዳንትነት ያቀረባቸው ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አስመራጭ ኮሚቴ መምረጥ እንደማይቻል ነው የተናገሩት።

 አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ እየተሰራበት ያለው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ "አይፈቅድም" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 በጉባኤው ላይ የቀረበው የተሻሻለው ረቂቅ መተዳዳሪያ ደንብ በአግባቡ ያልተጠናና ችግሮች የበዙበት ነው በሚል ሳይጸድቅ በመቅረቱ አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ እንደማይቻልም ጠቅሰዋል።

 የምርጫውን ጊዜ መራዘም ከማይፈልጉ አባላት መካከል የነበሩት ዶክተር አሸብር የመራዘሙ እውን መሆን ከተረጋገጠ በኋላ "መራዘሙ ለእኔ የምረጡኝ ቅሰቀሳ ለማድረግ ጥሩ ነው" ብለዋል።

 የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው አስመራጭ ኮሚቴ ለምን እንዳልተመረጠ ለቀረበላቸው ጥያቄ ''የጉባኤው አባላት ጠቅላላ ጉባኤው አልቋል ሳይባል ነው የተበተኑት'' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

 ይህ የሆነው በዋናነት አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚፈልጉና የማይፈልጉ የሁለት ጎራ አስተሳቦች በመፈጠራቸው እንደሆነም ነው የተናገሩት።

 አቶ ጁነዲን ጉባኤው በተጠናቀቀበት በትናንትናው ዕለት ከተቻለ ከሰዓት በኋላ አባላቱ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ጉዳዩ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል ቢሉም አስመራጭ ኮሚቴ የመምረጡ ጉዳይ ሳይቋጭ የጉባኤው አባላት ተበትነዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ