አርዕስተ ዜና

በቀሪ የአትሌቲክስ ዘመኔ በማራቶን ብቻ እወዳደራለሁ - አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ

09 Oct 2017
1227 times

አዲስ አበባ መስከረም 29/2010 በሴቶች ማራቶን ዓለም አቀፉን ሪከርድ መስበር ቀጣይ እቅዷ መሆኑን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አስታወቀች።

ጥሩነሽ ትናንት በቺካጎ የተዘጋጀውን የማራቶን ውድድር ካሸነፈች በኋላ እንዳለችው "በቀሪ የአትሌቲክስ ዘመኔ በማራቶን ሩጫ ላይ ብቻ ነው የምወዳደረው" ብላለች።

አትሌቷ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሠዓት ከ18 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ የፈጀባት ሲሆን በማራቶን ውድድር የመጀመሪያ ድሏ ነው።

በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናና ኦሎምፒክ ውድድሮች አንፀባራቂ ድሎች በማስመዝገብና የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት ጥሩነሽ ስኬታማ ጊዜ አሳልፋለች። 

 ከእነዚህ መካከልም እ.ኤ.አ 2017 በተካሄደው የለንደን ማራቶን 2 ሠዓት ከ17 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ የገባችበት ጊዜ የግል ምርጥ ሠዓቷ ነው።

 አትሌቷ እ.ኤ.አ 2003 እና 2005 በፈረንሳይ ፓሪስና በፊንላንድ በተካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎች አግኝታለች።

 እ.ኤ.አ 2005፣ 2007 እና 2013 በፊንላንድ ሄልሲንኪ፣ በጃፓን ኦሳካ፣ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችም የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ናት።

 በተመሳሳይ እ.ኤ.አ 2008 በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የድርብ ድል ባለቤት ስትሆን በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ በ10 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።

 በ2004 የአቴንስ፣ በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ውድድሮች በ5 ሺህ ሜትር፤ እንዲሁም በ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

 ከ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች በተጨማሪ በዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድሮች ለአገሯ አራት የወርቅና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማስገኘቷም የስኬቷ መገለጫ ነው።

 በትናንትናው የቺካጎ ማራቶን ከመጀመሪያው ኪሎ ሜትር ውድድሩ እስኪጠናቀቅ የመሪነቱን ስፍራ በመያዝ ማጠናቀቋን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል።

 አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በቀሪ የአትሌቲክስ ዘመኗ ማራቶን ላይ ብቻ እንደምታተኩርና ወደ ትራክ ውድድር እንደማትመለስ ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጋር በነበራት ቆይታ አስታውቃለች።

 "ማራቶኑን ያለ አሯሯጭ ነው የሮጥኩት፣ 42 ኪሎ ሜትሩን ወድድሩን በመምራት ነው ያጠናቀኩት፣ የመሮጫው ቦታ ሪከርድ ለመስበር የሚያመች ነበር ነገር ግን አየሩ ነፋሻማ በመሆኑ ማሳካት አልቻልኩም" ብላለች ጥሩነሽ።

 ውድድሩን በማሸነፏ ደስተኛ እንደሆነች ገልጻ "ከለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ለዚህ ውድድር የነበረኝ ጊዜ በቂ ባይሆንም  ጠንክሬ በመስራት ዝግጅት ሳደርግ ቆይቻለሁ" ነው ያለችው። 

 በትናንቱ ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮሴጊ 2 ሠዓት ከ20 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ በመግባት 2ኛ ስትወጣ አሜሪካዊቷ ጆርዳን ሀሳይ 2 ሠዓት ከ20 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ በማስመዝገብ 3ኛ ሆናለች።

 በወንዶች በተካሄደው ውድድር አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ በአንደኝነት ሲያሸንፍ ኬንያውያኑ አቤል ኪሩይ እና በርናንድ ኪፕዬጎ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ኢትዮጵያው አትሌት ሲሳይ ለማ አራተኛ ወጥቷል።

 በሌላ በኩል በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ በተካሄደው የ20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገበያነሽ አየለ 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ02 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ቀዳሚነቱን ይዛለች።

 ኬንያዊቷ አትሌት ሱዛን ጄፕቶ 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያዊቷ ጉደታ በቀለች 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ በመግባት ሶስተኛ ወጥታለች። 

 በወንዶች ውድድርም ኬንያውያኑ ኮሊንስ ቼቢ እና ጆስባት ኪፕሮኖ ሜንጆ እንዲሁም ፈረንሳዊው ፍሎሪያን ካርቫሎ በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት አሸንፈዋል።

 ለ40ኛ ጊዜ የተካሄደው የቺካጎ ውድድር በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ነው።

 በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ የሚካሄደው የ20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ደግሞ በማህበሩ የነሐስ ደረጃ ተሰጥቶታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ