አርዕስተ ዜና

የስታዲየም መግቢያ ሰልፍን የሚያስቀር ቴክኖሎጂ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል

05 Oct 2017
1215 times

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 በአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ትኬት ለመቁረጥ የሚፈጠረውን ረጅም ሰልፍ የሚያስቀር ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ሊያውል መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የፌዴሬሽኑ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ታፈሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቴክኖሎጂው ለዚሁ ስራ በሚከፈቱ ጣቢያዎች፣ በሞባይልና በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቅም ላይ ይውላል።

አሰራሩ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና ትኬት ለመቁረጥ ይፈጠር የነበረውን ረጅም ሰልፍ የሚያስቀር ነው።

እግር ኳስ መመልከት እየፈለጉ በትኬት መቁረጫ ወረፋ ሳቢያ ይቀሩ ለነበሩ ቤተሰቦች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርና ተመልካቾች ወደ ሜዳ እንዲመጡ የሚያበረታታም ነው ብለዋል።

ይህ አሰራር ክለቦች ከሜዳ ገቢ ጋር በተያያዘ ድርሻዬ ከደጋፊዎቼ ጋር የሚመጣጠን አይደለም በሚል የሚያነሱትን ቅሬታም ይፈታል ተብሏል።

በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚተገበረው አሰራር ባለሜዳው ክለብ በዕለቱ ምን ያህል ደጋፊቹ ወደ ሜዳ እንደገቡ የሚያውቅ በመሆኑ ገቢውን በራሱ መመዝገብ ይችላል።

አገልግሎቱ በዚህ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ሳምንት በሚካሄዱ ጨዋታዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

አዲሱ አሰራር ለጊዜው በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚጀመር ሲሆን በሂደት ወደ ክልሎች እንደሚስፋፋ ነው አቶ ኢሳያስ የተናገሩት።

ፌዴሬሽኑ አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ከተሰኘ ተቋም ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

አገልግሎቱን የሚሰጠው ክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ከትኬቱ ሽያጭ በሰው 8 በመቶ የሚያገኝ ይሆናል።

የአዲሱ አሰራር ወጪ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል ትኬት ለማሳተምና ለሽያጭ ሠራተኞች ይከፍል ከነበረው ኮሚሽን ጋር ተመሳሳይ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ