አርዕስተ ዜና

የስፖርት ፌዴሬሽኖች በስፖርቱ ባለፉ ሰዎች ሊመሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳሰቡ Featured

13 Sep 2017
1330 times

አዲስ አበባ መስከረም 3/2010 የስፖርት ፌዴሬሽኖች በስፖርቱ ውስጥ ባለፉ ሰዎች ሊመሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አሳሰቡ ።

ለአትሌት አልማዝ አያና እና ሙክታር እንድሪስ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ በስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

መንግስት በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የልዑካን ቡድን ውጤት እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ  እንደተናገሩት፤ ስፖርቱ በሙያው ባለፉና እውቀቱ ባላቸው ሰዎች ሊመራ ይገባል።

ይህን ለማድረግ  ክልሎች በየፌዴሬሽኖቹ የሚወክሏቸውን ሰዎች  ሲመርጡ ለስፖርቱ እድገት የሚበጀውን የተመራጮቹን ልምድ ከግምት ሊያስገቡ እንደሚገባ ገልጸው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን አወቃቀርና እየመጣ ያለውን ውጤት እንደምሳሌ አንስተዋል።  

በሥነ ስርዓቱ ላይ በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለአገራቸው ወርቅ ላመጡት አትሌት አልማዝ አያና እና ሙክታር እንድሪስ በአዲስ አበባ ከተማ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን ቦታ ተሰጥቷቸዋል።

በሻምፒዮናው በ10 ሺ ሜትር የወርቅ፤ በ5 ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያ ላስገኘችው ለአትሌት አልማዝ አያና 500 ካሬ ሜትር ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ  ተሰጥቷታል።

በወንዶች 5 ሺህ ሜትር የወርቅ  ሜዳሊያ ላመጣው ለአትሌት ሙክታር እንድሪስ ደግሞ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ተበርክቶለታል።

ሌሎች አትሌቶች፣ አሰልጣኞች እና ሌሎች የልዑካን ቡድኑ አባላትም እንዳስመዘገቡት ውጤት ገንዘብ ተሸልመዋል።

በሻምፒዮናው ብር ላስገኙ አትሌቶች 75 ሺ ብር፣ ዲፕሎማ ላስገኙ አትሌቶች ደግሞ 20 ሺ ብር  ሲሸለሙ ለተሳተፉት ደግሞ 10 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶቸዋል።

አሰልጣኞችም እንደ አመጡት ውጤት 60 ሺ፣ 35 ሺ እና 20 ሺ ብር ተሰጥቷቸዋል።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በወንዶች 5 ሺ ሜትር ውድድር ለቡድን ስራ ላበረከተው አስተዋጽኦ ልዩ ተሸላሚ በመሆን 50 ሺ ብር ተበርክቶለታል።

የአትሌት አልማዝ አያና ባለቤትና አሰልጣኝ ሶሬሳ ፊዳም ለአትሌቷ ውጤታማነት ድርሻው የጎላ በመሆኑ በልዩ ተሸላሚነት 60 ሺ ብር ተሰጥቶታል።

አትሌት አልማዝ ከሽልማቱ በኋላ እንደተናገረችው፤ ሽልማቱ ከአሌቲክሱ ልፋት ጋር ሲነጻጸር የሚገባ ቢሆንም፤ የቤት መስሪያ ቦታ እንዳልጠበቀች ነው የተናገረችው።

አትሌት ሙክታር እንድሪስም በበኩሉ ህዝቡ ላሳየው ክብርና አድናቆት አመስግኖ፤ ሽልማቱ በቀጣይ ለሚኖሩ ውድድሮች የሚያበረታታና ለሌሎች ስፖርቶችም መነቃቃት እንደሚፈጥር ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ከነሀሴ 28 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በተካሄደው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለት ወርቅና ሶሰት ብር ከዓለም ሰባተኛ ሆና እንድታጠናቅቅ አስተዋጽዖ ላደረጉት የልዑካን ቡድኑ አባላት የተሰጠው ማበረታቻ ሽልማት አንድ ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ