አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያ ቡና ለአዲሱ ዘመን አቀባበል የተዘጋጀውን ዋንጫ አነሳ

10 Sep 2017
1318 times

አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2009 የ2010 ዓ.ም አዲስ ዓመት አቀባበል በማስመልከት የተዘጋጀውን የእግር ኳስ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና ወሰደ።

አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ቁጥሬ ዱለቻ በታዋቂ አትሌቶች መካከል የተካሄደውን የ1 ሺ 500 ሜትር ሩጫ ውድድር አሸንፈዋል።

''መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ከፍታ ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ የ2010 ዓ.ም አዲስ ዓመትን አቀባበል በማስመልከት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂደዋል፡፡

በደጋፊ ብዛት የሚታወቁት የኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት እግር ኳስ ጨዋታ ውድድር በኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን በደጋፊዎቻቸው መካከል የነበረው አዝናኝ የድጋፍ አሰጣጥም የተመልካችን ቀልብ የሳበ ነበር።

በቀድሞዎቹ ታዋቂና አንጋፋ አትሌቶች መካከል በተካሄደው የ1ሺ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር በወንዶች ኃይሌ ገብረስላሴ በቀዳሚነት ሲያጠናቀቅ ገዛኽኝ አበራና አሰፋ መዝገቡ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።

አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ  ከሴቶች አሸናፊ ስትሆን፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ እና ጌጤ ዋሚ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።    

በዕለቱ የቦክስ፣ የገመድ ጉተታ፣ የጅምናስቲክ እንዲሁም ሌሎች አዝናኝ ስፖርታዊ ክልንውኖች ተካሂደዋል።

ውድድሩ መንግስት ከነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት ለእያንዳንዱ ቀን የተለያዩ ስያሜ በመስጠት ''መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ከፍታ ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ እያከበረ ያለው ዝግጅት አካል ነው።  

ስፖርታዊ ውድድሮቹን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በትብብር በጋራ ያዘጋጁት ነበር ።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ