አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ቢሮው በምዘና ውድድሩ 70 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በአንደኝነት ለማጠናቀቅ መዘጋጀቱን ገለጸ

10 Aug 2017
849 times

አዲስ አበባ  ነሐሴ 4/2009 በአምስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊዎች የምዘና ውድድር 70 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ለመሆን ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

 ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎችን የሚያሳትፈው ይኸው የምዘና ውድድር ከነሐሴ ሰባት ጀምሮ ለሁለት ሳምንት ያህል በ13 የስፖርት ዓይነቶች በሐዋሳ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

 ነገ ጠዋት ወደ ስፍራው ለሚያቀናውና 162 ወንድና 139 ሴት በድምሩ 301  ስፖርተኞችን ለያዘው የመዲናዋ የስፖርት ልዑካን ቡድን ዛሬ አሸኛኘት  ተደርጎለታል። 

 በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን ለሦስት ሳምንት ያህል በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ዝግጅት ማድረጋቸውን በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ገልጸዋል።

 ለቅድመ ሥራ ዝግጅቱ በተለያዩ ኮሚቴዎች  ክትትልና ድጋፍ  ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በሥልናም የታዩ ክፍተቶችን ማረም እንደተቻለ ነው የገለጹት።

 የተሰጠው ሥልጠና ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ በምዘና ውድድሩ 30 ወርቅ፣ 18 ብርና 12 ነሐስ በድምሩ 70 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በአንደኝነት ለማጠናቀቅ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል። 

 በፓራ ኦሎምፒክም 17 ወርቅ፣ 17 ብርና 13 ነሐስ በድመሩ 47 ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰብ ዝግጅት መደረጉን አቶ ዳኛቸው ጠቁመዋል።

 ለዕቅዱ ስኬታማነት ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ በቀጣይ ለአገሪቱ ተስፋ የሚጣልባቸው ስፖርተኞች የሚታዩበት የስፖርት መድረክ እንደሚሆንም ነው ያመለከቱት።  

 አሰልጣኞችና ስፖርተኞች በበኩላቸው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የመዲናዋን ስም ለማስጠራት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

 ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት አምስተኛው የታዳጊዎች የምዘና ውድድር ከመጪው ዕሁድ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ