አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በአምስት ሺህ ሜትር ተስፋ የተጣለባቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ

10 Aug 2017
1106 times

ነሃሴ 4/2009 በለንደን በመካሄድ ላይ በሚገኘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ሺህ ሜትር የወንዶች ማጣሪያ ሩጫ ውድድር የተሳተፉት አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሰለሞን ባረጋና  ሙክታር ኢድሪስ ለፍጻሜ ማለፋቸውን አረጋገጡ።

በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል የሴቶች ማጣሪያ ውድድር አትሌት እቴነሽ ዲሮና ብርቱካን ፈንቴ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገባቸው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለዋል።

አምስት ሺ ሜትር የወንዶች ማጣሪያ ውድድር ተሳታፊ የነበሩት አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻና ሰለሞን ባርጋ ከምድባቸው አንደኛ በመውጣት  ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለዋል።

ከመጀመሪያው ምድብ ዮሚፍ ቀጀልቻ አንደኛ ሲወጣ ሙክታር ኢድሪስ ሶስተኛ ሆኖ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በዓለም ሻምፒዮና መክፈቻ ውድድር በ10 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በዚሁ ምድብ ዮሚፍን ተከትሎ በሁለተኝነት አጠናቋል።

በሁለተኛው ምድብ የተወዳደረው  ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ከየምድባቸው ርቀቱን በአንደኝነት ያጠናቀቁት አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻና ሰለሞን ባርጋ በፍጻሜው እንደሚያሸንፉ ከወዲሁ ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

የአትሌት ዮሚፍ  የእግር አጣጣሉ፣ የአሯሯጥ ስልቱና ቴክኒኩ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እየተቸረው ነው።

በሪዮ ኦሎምፒክ በአምስት ሺ ሜትር ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚው አትሌት ሐጎስ ገብረሂወት በውድድሩ ላይ አለመካፈሉን አለም አቀፉ አትሌቲከሰ ፌዴሬሸን ማህበር በድረ ገጹ ላይ አሰነብቧል፡፡ ሐጎስ በውድድሩ ያልተሳተፈበት ምክንያት  አልተገለጸም።

የአምስት ሺ ሜትር የወንዶች ፍጻሜ ውድድር ቅዳሜ ከምሽቱ 4፡20 ይከናወናል።

ኢትዮጵያን ወክለው በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል የሴቶች ማጣሪያ ውድድር የተሳተፉት ብርቱካን ፈንቴና እቴነሽ ዲሮ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ለቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። አትሌት ሶፊያ አሰፋ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለችም፡፡

የሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ነገ ከምሽቱ  5፡25 ሰዓት ላይ እንደሚከናወን ከወጣው መርሃግብር ለማወቅ ተችሏል።

 በዛሬው ዕለት በተለያዩ ርቀቶች የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሔዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የ800 ሜትር ሴቶች፣ የ1ሺ 500 ሜትር ወንዶች  እና የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ዛሬ ምሽት 2፡30 ሰዓት በሚካሄደው የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ማጣሪያ በሻምፒዮናው በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ ያስገኘችው አትሌት አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ለተሰንበት ግደይና ሰንበሬ ተፈሪ ይካፈላሉ።

ከምሽቱ 3፡25 ሰዓት ላይ በሚጀምረው የ800 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ ውድድር ሃብታሙ አለሙ፣ ኮሬ ቶላና ማህሌት ሙሉጌታ ይሳተፋሉ።

የ1ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ከምሽቱ 4፡25 ሰዓት ላይ የሚጀመር ሲሆን፤አትሌት አማን ወጤ፣ ሳሙኤል ተፈራና ተሬሳ ቶሎሳ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

ኢትዮጵያ አንድ ወርቅና ሁለት ብር በድምሩ ሶሰት ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አሜሪካ በአራት ወርቅ በአምስት ብርና በስድስት ነሐስ አንደኛ፤ ኬንያ በሶስት ወርቅ አንድ ብርና ሶስት ነሐስ ሁለተኛ ፣ ደቡብ አፍሪካ በሁለት ወርቅና በሁለት ነሐስ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ከተጀመረ ሰባተኛ ቀኑን የያዘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ