አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን ሙሉ አባል የመሆን ጥያቄዋ ከአንድ ወር በኋላ ይመለሳል

19 Jun 2017
870 times

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2009 ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን ሙሉ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ከአንድ ወር በኋላ በቱርክ በሚካሂደው ጉባኤ መልስ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

በ23ኛው ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ተካፋይ እንድትሆን ጥሪ እንደቀረበላትም የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን አስታውቋል።

መስማት የተሳናቸው ስፖርት ውድድሮች በፓራ ኦሊምፒክ ስፖርት ሥር ሆነው ነበር ውድድሮችን ሲያካሂዱ የነበሩት።

የዓለም አቀፉ መስማት የተሳናቸው ስፖርት ፌደሬሽን መቋቋምን ተከትሎ ግን መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ከፓራ ኦሊምፒክ እንዲወጣ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽንም በቀድሞ ስፖርት ኮሚሽን በአሁኑ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ዕውቅና አግኝቶ በ2006 ዓም በፌደሬሽን መልክ ሊቋቋም ችሏል።

ፌደሬሽኑ ከ2007 ዓ ም ጀምሮ በአገር ውስጥ የተለያዩ ውድድሮችን በማድረግ ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን በጊዚያዊነት አባል መሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ መቆያ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን ጊዚያዊ አባል ሆና ቆይታለች።

የሙሉ አባልነት ጥያቄዋ ደግሞ ከሐምሌ 9 እስከ 11 ቀን 2009 ዓም በቱርክ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ ይወሰናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ማድረጓ፣ የአፍሪካ መስማት የተሳናቸው ኮንፌደሬሽን አባልና በኮንፌደሬሽኑ ለቦርድ አባልነት መመረጧ ሙሉ አባል እንድትሆን ያግዛታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ፌደሬሽን አባል ከሆነች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ትሳተፋለች፣ የቁሳቁስና የሙያ ድጋፍም ታገኛለች።

ከጠቅላላ ጉባኤው በተጨማሪ 23ኛው ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ሻምፒዮና ከሐምሌ 11 እስከ 23 ቀን 2009 ዓም በቱርክ ይካሄዳል።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ተካፋይ እንድትሆን ከዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌደሬሽን ጥሪ ቀርቦላታል።

በውድድሩ ለመካፈልም በአትሌቲክስ ስፖርት የተሻለ ሰዓት ያላቸው ስድስት መስማት የተሳናቸው አትሌቶች ተመርጠው በግላቸው ልምምድ እየሰሩ ነው ብለዋል ኃላፊው።

ከስድስቱ አትሌቶች መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ