አሶሴሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በጃንሜዳ የመኪና ውድድር አካሄደ

18 Jun 2017
736 times

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2009 የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ያዘጋጀው የመኪና ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ተካሄደ። ውድድሩ በጃንሜዳ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በዕለቱ ውድድሩን ሲመለከቱ በነበሩ ስድስት ተመልካቾች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

በማወዳደሪያ ችግርና ተወዳዳሪዎች የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ምክንያት ወጥ የሆነ የሞተር ስፖርት ውድድር ማድረግ አልተቻለም ነበር።

ዛሬ ከአንድ ዓመት በኋላ በአምስት ምድብ በተካሄደው ውድድር 21 የመኪና ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

ብርቱ ፍክክር በታየበትና ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት አምስተኛ ምድብ  ጣሊያናዊው ኤርነስቶ ሞሊናር አሸናፊ ሲሆን፣ በመኪናና በሞተር ውድድር በርካታ ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊው አንተነህ ተጫኔ ሁለተኛ ወጥቷል።

በዚህ ምድብ የተወዳደረው ዮናስ እጅጉ ደግሞ ሶስተኛ ሆኗል።

በአራተኛው ምድብ ጣሊያናዊው ሲሞን ፈራሪ አንደኛ፤ ኢትዮጵያዊው ሄርኩለስ ሙጂ ሁለተኛ በመሆን አሸንፈዋል።

ጣሊያናዊው ሶርጆ ኦሊቨሮ አንደኛ፣ ሀሽም አቦበከር ሁለተኛ በመሆን የሶስተኛው ምድብ አሸናፊዎች ናቸው።

በአንደኛ ምድብ ፋህሚ ግርማ አንደኛ፣ አሚር ሸምሱ ሁለተኛ፣ ፍቃዱ ከበደ ሶስተኛ ሲሆኑ፤ በሁለተኛው ምድብ ፋኑኤል ታምራትና ኩሩቤል ፉፋ በተከታታይ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ማሸነፍ ችለዋል።

በዕለቱም አሸናፊ ተወዳዳሪዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላችዋል።

የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደተናገሩት፤ በማዘወተሪያ ስፍራ እጥረት የመኪና ውድድሮች ሳይካሄዱ ቆይተዋል።

ዛሬ በጃንሜዳ የመኪና ውድድር መደረጉ "ለስፖርቱም ሆነ ለተወዳዳሪዎች መነቃቃት የሚፈጥር ነው" ብለዋል።

በዕለቱ ሁለት ተወዳዳሪዎች ለአሸናፊነት ሲፎካከሩ የአንደኛው መኪና ከውድድር ማብቂያ ቦታ ዘሎ በመውጣት በስድስት ተመልካቾች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ተመልካቾች ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና ከተከታተሉና ምንም ዓይነት የከፋ ችግር እንዳላጋጠማቸው ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

በውድድሩ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታና ሌሎች ኃላፊዎች ተገኝቷል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ