ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ የስፖርት ሳይንስ ተማሪዎች የክህሎት ምዘና ያስፈልጋል

16 Jun 2017
735 times

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 በስፖርት ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎች ለማፍራት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የስፖርት ሳይንስ ተማሪዎች ክህሎት ሊመዘን እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

የመግቢያ ውጤት አስመዝግበው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ የሚመደቡት ባላቸው የስፖርት ክህሎት ሳይሆን በፍላጎታቸው ነው።

ይህ መሆኑ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ከሚወጡ የመስኩ ባለሙያዎች አብዛኛዎቹ የስፖርት እንቅስቃሴ ክህሎት ይዘው እንዳይወጡ  ማድረጉን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል።

ምሩቃኑ ለአገሪቱ ስፖርት እድገት በሙያቸው እገዛ ማድረግ ቢጠበቅባቸውም በክህሎት የበለጸጉ ባለመሆናቸው እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳልቻሉ ነው የስፖርት ምሁራኑ የገለጹት።

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ዲን ዶክተር አብነት አያሌው እንደተናገሩት ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ማፍራት ያልተቻለው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ ተሰጥኦና ክህሎትን መሰረት ያደረገ ምዘና ባለመኖሩ ነው።

ስፖርት በተግባር የሚታይ በመሆኑ ሰልጣኞቹ በዘርፉ ያላቸው ክህሎትና ተሰጥኦ በተግባር ተመዝኖ እንዲገቡ በማድረግ ሳይንሳዊ እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።

"ይህ ባለመሆኑ ምሩቃኑ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም" ያሉት ዶክተር አብነት በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ዘርፍ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች የክህሎት ፈተና እንዲወስዱ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

"በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በስፖርት ዘርፍ የሚሰጠው ስልጠና ወጥ እንዲሆን የጋራ የመመዘኛ መስፈርት ቢወጣ መልካም ነው" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

"ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ የስፖርት ባለሙያዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ችግር ይስተዋልባቸዋል" ያሉት ደግሞ የአዳማ ዮኒቨርሲቲ የስፖርት መምህር ይገርማል ንጉሴ ናቸው።

እንደ እሳቸው ገለፃ በስፖርት ሳይንስ ከሚሰለጥኑ ተማሪዎች አብዛኞቹ ፍላጎት የሌላቸውና ከአንድ የአካል ብቃት ባለሙያ የሚጠበቀውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ አይደሉም።

የስፖርት ፍላጎትና ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች በማሰልጠን በዘርፉ በማሰማራት የአገሪቱ ስፖርት ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር አስጨናቂ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በ1994 ዓ.ም የራሱን ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ የተግባር ፈተና በመስጠት የስፖርት ስልጠና መጀመሩን አስታውሰዋል።

ሆኖም ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ክፍሉ እንደ ሌሎች ትምህርት ክፍሎች በአገር አቀፍ የስርዓተ ትምህርት በመካተቱ ያለ ተግባር ፈተና የፍላጎት ምደባ መጀመሩን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ በስፖርት ሳይንስ ሰልጥነው ለሚወጡ ተመራቂዎች የተግባር ክህሎት ደካማ መሆን ምክንያት እንደሆነ ነው የገለጹት።

በቀጣይ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከተመደቡ ተማሪዎች መካከል በተግባር ፈተና በመለየት በስፖርት ሳይንስ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን ዶክተር አስጨናቂ ተናግረዋል።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ