በፈረንሳይ በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ

16 Jun 2017
625 times

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 በፈረንሳይ ላንግል በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ።

በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የነሐስ ደረጃ ያለው 27ኛው የኮሪዳ ላንግል የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ነገ ይካሄዳል።

በዚህ ውድድር የአምና አሸናፊዋ አትሌት መስከረም አማረ ክብርዋን ለማስጠበቅ ትሮጣለች።

አትሌት መስከረም ባለፈው ዓመት 32 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ከ16 ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝገብ በአንደኝነት ማጠናቀቋ ይታወሳል። ዘንድሮም ክብሯን ላለማስነካት ብርቱ ተፎካካሪ ትሆናለች።

ከሁለት ዓመት በፊት 31 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ በመግባት የቦታው ክብረወሰን መያዝ የቻለችው ኬንያዊቷ አትሌት ግላድያስ ያቶር የመስከረም ተቀናቃኝ እንደምትሆን ይጠበቃል።

በወንዶች ምድብ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሀይማኖት አለው በውድድሩ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል።

ሃይማኖት በ2017ት ካደረጋቸው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድሮች መካከል 28 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ በመግባት የግሉ ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

በ2014 በተደረገው የላንጉል ውድድር ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው በትውልድ ኢትዮጵያዊው በዜግነት ባህሪናዊው አትሌት ዳዊት ፍቃዱ በወንዶች ምድብ ይጠበቃል።

በርቀቱ 28 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ ያለው ኬንያዊው ፓትሪክ ሙታንጋም በውድድሩ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በኖርዌይ ኦስሎ በተደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያቷ አትሌት ሶፍያ አሰፋ በሶስት ሺ ሜትር መሰናክል ሁለተኛ ወጥታለች።

ሶፍያ ውድድሩን ለመጨረስ 9 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ከ34 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶባታል።

ኬንያዊቷ አትሌት ጄሪቶ ኖራህ ውድድሩን በአንደኝነት ስታጠናቅቅ ፤ ስዊዘርላንዳዊቷ ሹልምፔ ፋብኔ በሶስተኝነት አጠናቃለች።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ