ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሄንግሎ የሠዓት ማሟያ ውድድር ተካሄደ

12 Jun 2017
1070 times

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2009 በመጪው ሐምሌ መጨረሻ በለንደን በሚካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ለመምረጥ የሠዓት ማሟያ ውድድር በኔዘርላንድስ ሄንግሎ ተካሄደ።

ውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኤፍ.ቢ.ኬ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በተደረገው የሠዓት ማሟያ ውድድር አትሌት ገለቴ ቡርቃ 30 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ከ87 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አንደኛ ወጥታለች።

ሰንበሬ ተፈሪ 30 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ68 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ስትሆን፤ በላይነሽ ኦልጅራ ከሰንበሬ በሶስት ሰከንድ ዘግይታ ሶስተኛ በመውጣት ሚኒማ አሟልተዋል።

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት አባዲ ሀዲስ 27 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ ከ26 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አንደኛ ወጥቷል።

ጀማል መኮንን 27 ደቂቃ ከ9 ሰከንድ ከ8 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ፤ አትሌት የኔዋላ አመራው በ27 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል።

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች አትሌት ሶፊያ አሰፋ ውድድሩን በ9 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ ከ06 ማይክሮ ሰከንድ በማጠናቀቅ የራሷን ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸንፋለች።

አትሌት ብርቱካን አዳሙ በ9 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ ከ67 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ሆናለች።

በወንዶች አትሌት ጌትነት ዋሌ በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ 8 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ከ28 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶበታል።

ታፈሰ ሰቦቃ 8 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ከ22 ማይክሮ ሰከንድ በሁለተኝነት ሲያጠናቅቅ ጫላ በዮ በ8 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ከ24 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል።

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች ውድድር ከአንደኛ እስከ አራተኛ የወጡ አትሌቶች የራሳቸውን ምርጥ ሠዓት በማስመዝገብ ጭምር ነው ያሸነፉት።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት ሳሙኤል ተስፋዬ በ3 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ከ78 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል።

አማን ወጤ ሁለተኛ፤ ተሬሳ ቶሎሳ ሶስተኛ በመሆን አሸንፈዋል።

በ1 ሺህ 500፣ በ3 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ያሸነፉና በሌሎች ርቀቶች ሚኒማ ማምጣት የቻሉ አትሌቶች በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ታምራት ቶላና ጸጋዬ መኮንን፤ በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ማሬ ዲባባና ሹሬ ደምሴ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የማራቶን ሯጮች መሆናቸውን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ