አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ያስጠሩ ሴት ስፖርተኞችና አመራሮች ዕውቅና ተሰጣቸው Featured

19 May 2017
916 times

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ላስጠሩ ሴት ስፖርተኞችና የአመራር አባላት ዕውቅና ተሰጠ። 

የዕውቅና ፕሮግራሙን ኢ-መልቲ ሚዲያ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኦሊምፒክ ኮሚቴና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።

በስፔን ባርሴሎና በተካሔደው የኦሊምፒክ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው የአፍሪካ ቀዳሚዋ እንስት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ እውቅናው ከተሰጣቸው መካከል ነች።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1996 በአሜሪካ አትላንታ በተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን በኢትዮጵያ ታሪክ ወርቅ ያስገኘችው አትሌት ፋጡማ ሮባም ተካታለች።

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የፕሪሚየር ሊግ የወንዶች ክለብ በማሰልጠን የመጀመሪያዋ፤ ድሬዳዋ ከነማ ከብሄራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ያደረገችው አሰልጣኝ መሰረት ማኔም ዕውቅና አግኝታለች።

ኢትዮጵያን በመወከል የአፍሪካና የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ውድድሮችን በዳኝነት የመራችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰም ዕውቅና የተሰጣት ሌላዋ እንስት ነች።

በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በቴኳንዶ ስፖርት ወርቅ ያስገኘችው ዮርዳኖስ ሲሳይ፣ የብስክሌት ስፖርት ተወዳዳሪዋ ኢየሩሳሌም ዲሮ ዕውቅና ከተሰጣቸው ወጣት ሴት ስፖርተኞች መካከል ናቸው።

በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ አካዳሚ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ማሞና የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚዋን ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይን ጨምሮ በአመራርነት ደረጃ የኢትጵያን ስፖርት ለማሳደግ ጉልህ ሚና የተጫወቱ እንስቶችም የዕውቅናው ባለቤቶች ሆነዋል።

በዕውቅና ፕሮግራሙ የህጻናትና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርስን ጨምሮ በርካታ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ስፖርትና የሴቶች ሚና በሚል ርዕሰ ጉዳይም ውይይት ተካሂዷል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ