አርዕስተ ዜና

የሁለቱ ከነማዎች ጨዋታ በድሬ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

19 May 2017
863 times

ድሬዳዋ ግንቦት 10/2009 በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ድሬ ከነማ በሜዳው ሃዋሳ ከነማን አንድ ለዜሮ አሸናፈ፡፡

በ35ኛው ደቂቃ ላይ ያገኛትን የፍፁም ቅጣት ምት 7 ቁጥሩ ሱራፌል ዳንኤል አስገብቶ  ነው ድሬ  ሃዋሳን ማሸነፍ የቻለው፤ የፍፁም ቅጣት ምቱ ትክክል አይደለም በሚል የሃዋሳ ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ተጫዋቾቹ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም ዳኛው አሰልጣኙን ከተመልካቹ ጋር ጨዋታውን እንዲከታተሉ አድርገዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር፡፡

በመጀመሪያው ግማሽ የተሻለ ወደ ግብ መቅረብና የግብ እድል መፍጠር የቻለው ድሬ ከነማ ሌላ ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡

በሁለተኛው ግማሽም ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ ጨዋታው ውጥረት የተሞላበት፣ ፍትጊያ የተስተናገደበትና ምንም ጎል ያልተቆጠረበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡ 

ድሬ ከነማ በማሸነፉ ነጥቡን 31 በማድረስ ደረጃው ማሻሻል ቢችልም ከፕሪሚየር ሊጉ ላለመውረድ በቀሩት ሁለት ሣምንታት ፋሲልን ጎንደር ላይ ጅማ አባቡናን ድሬዳዋ ላይ  የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በውጤት መደምደም ይጠበቅበታል፡፡

የድሬዳዋ ከነማ ቡድን አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው " በጨዋታው ባገኘነው ሶስት ነጥብ ተደስቻለሁ፤ ውጤቱም ይገባናል" ብለዋል፡፡

ቡድኑ "በፕሪሚየር ሊጉ እንዲዘልቅ ጎንደርና ድሬዳዋ ላይ ስድስት ነጥብ ለማግኘት ነው የምንሰራው "ብለዋል፡፡

የሃዋሳው ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ "ዛሬ  ውድድሮች በተመሣሣይ ሰዓት እንዲካሄዱ መደረጉ ጥሩ ቢሆንም እንደነዚህ ዓይነት ወሳኝ ጨዋታዎችን በተሻሉና በቁንጮ ዳኞች መመራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

" ልጆቼ እንደልባቸው እንዳይጫወቱ ጫና ነበረባቸው፤ የተሰጠብንም ፍፁም ቅጣት ምት ተገቢ አይደለም፤ በተቃራኒው ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች ተከልክለናል" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለመጠናቀቅ የሁለት ሣምንት ዕድሜ በቀረው የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታው ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር እንደቀጠለ ሲሆን ዛሬ ውድድሩን የተመለከቱ በሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ቡድናቸው ሶስት ነጥብ በማግኘቱ ደስታቸው በየአደባባዩ እየገለፁ ናቸው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ