አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወላይታ ዲቻን አሸነፈ

18 May 2017
897 times

ሶዶ ግንቦት 10/2009 በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪመየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ ንግድ ባንክ ወላይታ ዲቻን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት አሸነፈ፡፡

የሁለት ጨዋታዎች ዕድሜ  በቀረው የፕሪምየር ሊጉ ፉክክር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲቻን ያሸነፈው  ዛሬ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ነው፡፡

ንግድ ባንክ ጎላን ያስቆጠረው የጨዋታው ሰዓት አልቆ በባከነው ደቂቃ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ ነው፡፡

ጎላን ያስቆጠረው የዲቻ ተከላካዮችን መዘናጋት የተጠቀመው ሁለት ቁጥሩ ፍቅረየሱስ ገብረ መድህን ነው፡፡

ሁለቱም ቡድኖች የመውረድ ስጋት ውስጥ ሆነው ያደረጉት ጨዋታ በመሆኑ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ወደጎል የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ ባንክ የተሻለ ነበር፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ ተጭነው በመጫወት በ78ኛውና 83ኛው ደቂቃ  በፈቱዲን ጀማል ሞክረው የባንኩ በረኛ ያወጣቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በ80ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ የዲቻ በረኛም ጭምር የወጣበትን አጋጣሚ ባንኮች መጠቀም ቢችሉ የጎል ልዩነቱ ሊሰፋ ይችል ነበር፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ዲቻ በኳስ ቁጥጥር በማጥቃትና በማደራጀት ለጎል  የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርግም ኢላማቸውን ባለመጠበቃቸው ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

በ54ኛው ደቂቃ ላይ የባንኩ 88 ቁጥሩ ታዲዮስ ወልዴ በዲቻው 19 ቁጥሩ አላዛር ፋሲካ ላይ በፈጸመው ያልተገባ አጨዋወት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ "ተመጣጣኝ ጨዋታ አሳይተናል ኳስ ይዘን በመጫወት ነጥብ ይዘን ለመመለስ ነበር፤ ተሳክቶልናል" ብለዋል፡፡

"የወላይታ ዲቻ በረጃጅም ኳሶችና በፈጣን ሩጫ የሚያስቸግር ቡድን በመሆኑ የተገኙ አጋጣሚዎችን መጠቀም ወሳኝ ነበር "ያሉት አሰልጣኝ ሲሳይ በውጤቱም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ዲቻ ቡድን ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ "በርካታ የጎል ዕድሎችን በሁለቱም የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብንፈጥርም ለማሸነፍ በነበረን ጉጉት የተነሳ ወደጎል  መቀየር ባለመቻል ተሸንፈናል " ብለዋል፡፡

መሸነፋቸው  በኳስ  ዓለም እንደሚያጋጥም የተናገሩት  አሰልጣኝ መሳይ "ከመውረድ ለመትረፍ ዕድሉ በእጃችን ያለ በመሆኑ ቀጣይ ያሉን ጨዋታዎች የምናሸንፍበት መንገድ ማሰብ ተገቢ ነው "ብለዋል

ዲቻ ቀሪ ጨዋታዎች አንዱን ከሜዳ ውጪ ከአርባ ምንጭ ከተማ የመጨረሻውን ደግሞ በሜዳው ከደደቢት ጋር ይገጥማል፡፡

በተለይ በተጨማሪ ሰዓት ጎል ከገባ በኋላ  የዲቻ ደጋፊዎች ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር ለታዳጊ ወጣቶችና ለስፖርቱ ዕድገት አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ