አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች መድሃኒት ናሙናዎችን እያስመረመረች ነው

18 May 2017
774 times

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የጸረ-አበረታች መድሃኒት ምርመራ ዕቅድን ለማሳካት 160 ናሙናዎችን በፈረንሳይ እያስመረመረች ነው።

የዓለም አቀፍ የጸረ አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ (ዋዳ) በአትሌቶችና በሌሎች ስፖርተኞች ላይ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል።

አሁን ግን አገራት ብሄራዊ የጸረ- አበረታች መድሃኒት ጽህፈት ቤት አቋቁመው የሽንትና የደም ናሙና አሰባስበው በዋዳ ዕውቅና በተሰጣቸው የምርመራ ማዕከላት /ላብራቶሪ/ እንዲያሰሩ አዟል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጽህፈት ቤት በማቋቋምና በርካታ ገንዘብ በመመደብ የተለያዩ ናሙናዎች በመሰብሰብ በደቡብ አፍሪካና በኳታር የምርመራ ማዕከላት ስታሰራ ቆይታለች።

ነገር ግን ዋዳ በደቡብ አፍሪካና በኳታር የምርመራ ማዕከላት ላይ ዕገዳ መጣሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአትሌቶቿ የሰበሰበቻቸውን ናሙናዎች ወደ ፓሪስ በመላክ እያስመረመረች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች መድሃኒት መካላከልና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ለኢዜአ እንደገለጹት የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እስከ ሰኔ 2009 ዓም ድረስ የጸረ-አበረታች መድሃኒት ምርመራና የግንዛቤ ስራዎች እንዲሰሩ ዕቅድ አስቀምጧል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካትም በውድድርና ከውድድር ውጪ የ160 አትሌቶች የደምና የሽንት ናሙናዎችን በመሰብሰብ ወደ ፓሪስ ተልኮ እየተመረመረ ነው ብለዋል።

እቅዱ የተያዘው በ120 አትሌቶች የጸረ-አበረታች ምርመራ ለማድረግና የግንዛቤና የአስተዳደራዊ ስራዎች እንዲሰሩ ነው።

ዳይሬክተሩ "የዶፒንግ ምርመራን አሳክተናል፣ በግንዛቤ ስራው ግን ገና አንድ መድረክ ይቀረናል፤ ይህንንም በአጭር ጊዜ እናሳካዋለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ፓሪስ የላከቻቸው ናሙናዎችን ለማስመርመር ለአንድ አትሌት እስከ 200 ዩሮ ትከፍላለች።

ምንም እንኳን በጀቱ ከፍተኛ ቢሆንም በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ለመወዳደር የፀረ-አበረታች መድሃኒት መስፈርትን ማሟላት ግድ በመሆኑ በጀት መድበን እየሰራን ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ80 አትሌቶች ናሙና ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ20 በላይ ከሚሆኑ አትሌቶች ናሙና መሰብሰቡንም ነው አቶ መኮንን የገለጹት።

ምርመራው ከአትሌቲክስ ስፖርት በተጨማሪ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶችም እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ