አርዕስተ ዜና

አገር አቀፍ የስፖርት ጨዋታዎች ደረጃቸውን ባለመጠበቃቸው ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት አልተቻለም

17 May 2017
889 times

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2009 አገር አቀፍ የስፖርት ጨዋታዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ባለመካሄዳቸው ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት እንዳልቻለ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ለስፖርት ማህበራትና ለክልሎች የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊዎች በአገር አቀፍ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ዙሪያ ያካሄደውን መነሻ ጥናት አቅርቧል።

የጥናቱ አቅራቢ አቶ አስመራ ግዛው በአገሪቱ የሚካሄዱ የስፖርት ጨዋታዎች የሚፈለገውን ውጤት ላለመገኘቱ ምክንያቶች ያሏቸውን ዘርዝረዋል።

ከምክንያቶቹ የመጀመሪያው ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት።

የአዘጋጅ ክልልና የስፖርት ማህበራት አለመቀናጀት፣ ከአዘጋጁ በኩል ግልጽ የኮሚቴ አደረጃጀት አለመኖርና የአገር አቀፍ ውድድሮችን ዓላማ በግልጽ አለመረዳትም እንዲሁ።

በተለይም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የታዳጊዎች የምዘና ውድድሮች ላይ ቀድመው ያልሰሩትን የቤት ስራ ውጤት በአቋራጭ ለማግኘት መሞከር ለውጤቱ መቀነስ በጥናቱ የተለዩ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

በቀጣይ ደረጃውን የጠበቀ አገር አቀፍ ስፖርታዊ ጨዋታ ለማዘጋጀት ከእስካሁኑ አሰራር ወጥተው የራሳቸውን ማህበር ወይም ፌደሬሽን ማቋቋም እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የፋይናንስ አቅማቸውን ለማጎልበት የስፖንሰር፣ የምስል መብት፣ የትኬት ሽያጭና ሌሎች የገቢ ምንጮችን በመጠቀም ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባቸው አቶ አስመራ ጠቁመዋል።

በመላ ኢትዮጵያና በአገር አቀፍ የተማሪዎች ጨዋታዎች፤ በታዳጊ ወጣቶች ተሳትፎና አገር አቀፍ የሴቶች ተሳትፎ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ዝግጅት ማድረግ አለባቸውም ብለዋል፡፡ 

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ የመነሻ ጥናቱ በስፖርት ማህበራት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዛሬ የተጀመረው የስፖርት ተሳትፎ የውድድር አሰራር ስርዓት አተገባበር ለ3 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በማዘውተሪያ ቦታዎች ደረጃ አመዳደብ ደንብ፣ በስፖርት አመራርነት የሴቶች ሚናና የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና አፈጻጻም ላይ ውይይት ይካሄዳል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ