አርዕስተ ዜና

የክልሉን ስፖርት ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

20 Apr 2017
694 times

መቀሌ ሚያዝያ 12/2009 በትግራይ ክልል እየተቀዛቀዘ የመጣውን የስፖርት እንቅስቃሴ ቀድሞ ወደነበረበት ገጽታ ለመመለስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ ።

የክልሉ 24 ኛው የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ትናንት በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ኃይለ አስፋሃ እንደገለጹት፣ በክልሉ በስፖርት ዘርፍ እየታየ ያለውን የመቀዛቀዝና የውጤት ማሽቆልቆል ችግር ለመፍታት በትኩረትና በቅንጅት ሊሰራ ይገባል።

ለስፖርት እንቅስቃሴው በጀት መመደብ ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ልዩ አማካሪው በስፖርት ምክር ቤቶችና ፅህፈት ቤቶች ብቃት ያላቸውን አመራሮችና የስፖርት ባለሙያዎችን መመደብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የጉባኤው አባላት በበኩላቸው በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ  ስም ሊያስጠሩ የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎይተኦም ይብራህ በበኩላቸው የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ለስፖርቱ የሚያስፈልገው ገንዘብ እንዲሰበሰብ ትኩረት ሰጥተው አለመስራታቸው ለስፖርቱ እንቅስቃሴ መዳከም ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል ።

በተቃራኒው ለዘርፉ መጠናከር በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርትና የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ተቋማት እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ለሌሎች አርአያ መሆኑን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ለስታዲየም ግንባታ የሚውልና ለተለያዩ የስፖርት አይነቶች የውድድር ትጥቅ መግዥ 127 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተርና የአገር አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከሳቴ ለገሰ በበኩላቸው፣ የክልሉን የስፖርት እንቅስቃሴ ለማጠናከርና በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይ  በገንዘብና በማዘውተሪያ ስፍራ ግንበታ ያሉ ክፍተቶችን ፈጥኖ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

እንደ ዶክተር ከሳቴ ገለጻ በክልሉ በቀበሌ ደረጃ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ እንዲኖር ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ።

በክልሉ ከአንደኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉ የትምህርት ተቋማት በተግባር የተደገፈ የስፖርት ትምህርት ከመስጠት ባለፈ ወጥነት ያለው የስፖርት ውድድር በማካሄድ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

በጉባኤ ላይ 200 የሚሆኑ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የስፖርት አሰልጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸው ታውቋል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ