አርዕስተ ዜና

የሻሸመኔ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ለአንድ ዓመት ታገደ

20 Apr 2017
495 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009 የሻሸመኔ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ያሬድ አበጀ ከማንኛውም አይነት የእግር ኳስ ስፖርት እንቅስቃሴ ለአንድ ዓመት ታገደ ፤ ተጨማሪ የ15 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔም ተላለፈበት።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 17ኛ ሳምንት ውድድር ሆሳዕና ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከሻሸመኔ ከተማ ሲጫወቱ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዲሲኘሊን ኮሚቴ በክለቦችና ተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በወቅቱ ዋና ዳኛውን የመታውና ተጫዋቾች ዳኛው ላይ አደጋ እንዲያደርሱ ያነሳሳው የሻሸመኔ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ያሬድ አበጀ ከማንኛውም አይነት የእግር ኳስ ስፖርት እንቅስቃሴ የአንድ ዓመት እገዳና የ15 ሺህ ብር ቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል።

የቡድኑ ተጫዋች በኃይሉ አባተም ዳኛውን ለመደብደብና በስለት ለመውጋት በመሞከር በፈጸመው ከፍተኛ የስነ ምግባር ጥሰት ለስድስት ወራት ከጨዋታ እንዲታገድና 15 ሺህ ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

አሸናፊ ከበደና ሰለሞን ሽታ ደግሞ ዳኛው ላይ በድንጋይ አደጋ ለማድረስ በመሞከከርና ከፍተኛ የዲሲኘሊን ጥፋት በመፈፀም እያንዳንዳቸው ለስድስት ወራት ከጨዋታ ታግደው 15 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ዋና ዳኛውን ለመደብደብ የሞከረው የቡድኑ አምበል አብዮት ወንድይፍራውም የተጋጣሚውን ቡድን ተጫዋች በመማታቱና ከሜዳ አልወጣም በማለቱ ለስድስት ወራት እንዳይጫወት እገዳና የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎበታል።

በዚህ ጨዋታ የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች በፈጠሩት ሁከትና ብጥብጥ ጨዋታው ለ15 ደቂቃ እንዲቋረጥ ምክንያት በመሆናቸው ክለቦቹ እያንዳንዳቸው 25 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተወስኗል።

የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ በ10 ቀናት ለፌዴሬሽኑ ገቢ ካልሆነ ክለቦቹ በቀጣዮቹ ውድድሮች እንዳይሳተፉ የሚደረግ መሆኑን የዲሲኘሊን ኮሚቴው አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ''ለ'' የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማና ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አምስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ