አርዕስተ ዜና

ወላይታ ዲቻ ሀዋሳ ከነማን 1 ለ 0 አሸነፈ

19 Apr 2017
582 times

ሶዶ ሚያዚያ 11/2009 የ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ በሜዳው ሀዋሳ ከነማን የገጠመው ወላይታ ዲቻ አንድ ለዜሮ አሸነፈ።

የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የተጨመረው ደቂቃ ሊያልቅ የዳኛ ፉሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ 13 ቁጥሩ ዳግም በቀለ የወላይታ ዲቻዎችን ጎል አስቆጥሯል።

በመጀመሪያዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ  ኳስ  አደራጅቶ በመጫወት ሜዳዉን በመቆጣጠርና ወደ ጎል የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ የሃዋሳ ከነማ ቡድን የተሻለ ነበር።

ወላይታ ዲቻዎች ያገኙትን ኳስ ወደ ተቃራኒው ቡድን ሜዳ በማድረስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኢላማቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸዉ ወደ ጎልነት ሳይቀየሩ እስከ 47ኛ ደቂቃ ሊጠብቁ ግድ ብሏቸው ነበር።

በሁለተኛዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ባለሜዳዎች ተጭነዉ በመጫወት ሜዳውን ቢቆጣጠሩም ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል፡፡

ሃዋሳዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት ወደ ጨዋታው ለመመለስና ልዩነቱን ለማጥበብ ቢሞክሩም በተጋጣሚያቸው ተበልጠው አምሽተዋል፡፡

በርካታ ደጋፊ በስታዲየሙ ተገኝቶ ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ቡድኑን ሲያበረታታና ሲደግፍ ነበር።

የሃዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ “የልጆቼ ያለመረጋጋት ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ጎል ለመቀየር ያለመቻላችንና የሜዳው አለመመቸት የሽንፈታችን ምክንያት ነው” ብለዋል፡፡

“በመጀመሪያዉ ክፍለ ጊዜ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል በሁለተኛዉ ግን መድገም አልቻልንም ድቻ የተሻለ ነበር ማሸነፍ ይገባቸዋል” ሲሉ ለተጋጣሚያቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የደጋፊውን የድጋፍ አሰጣጥና ስነ-ምግባር ያደነቁት አሰልጣኝ ውበቱ የፍጹም ቅጣት ይገባን ነበር ሲሉ በዳኝነቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ዲቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ቡድናቸው በማሸነፉ መደሰታቸውን ገልጸው “ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ብንችል የጎል ልዩነቱ ሊሰፋ ይችል ነበር” ብለዋል፡፡

ተጋጣሚያችን ጥሩ ኳስ  ፍልስፍና የሚከተል በመሆኑ እስከ መጨረሻው ድረስ በማስጨነቅና አጥቅቶ ለመጫወት መግባታቸውን የተናገሩት አሰልጣኙ ከምንም በላይ በጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዘው መውጣታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ