አርዕስተ ዜና

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ጁባ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሊያካሂድ ነው

20 Mar 2017
879 times

አዲስ አበባ  መጋቢት 11/2009 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለችግር የተጋለጡ ደቡብ ሱዳናዊያንን ለመደገፍ በጁባ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ሊያካሂድ ነው።

መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በአገሪቷ መዲና ጁባ የሚካሄደው ውድድር በድርቅና በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ ማሰባሰብን ዓላማ ማድረጉን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

ውድድሩ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ነዋሪነቱን በደቡብ ሱዳን ባደረገው ኢትዮጵያዊ ባለሀብት አቶ አይሸሹም ተካ ነው የተዘጋጀው።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ "ስፖርት የፍቅርና የመረዳዳት መሳሪያ በመሆኑ የተቸገሩ የጎረቤት አገር ዜጎችን ለመርዳት አስበናል" ብሏል።

ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ከመርዳት ባሻገር ስለ ሠላም አስፈላጊነት መልዕክት ማስተላለፍና የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ሌላው የውድድሩ ዓላማ መሆኑን ገልጿል።

"ሠላም ከሁሉም ይበልጣል" ያለው ኃይሌ "የጎረቤት አገር ሠላም አለመሆን እኛንም የሚነካ በመሆኑ ደቡብ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሠላሟ እንድትመለስ በጋራ መስራት ይገባል" ብሏል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ውድድሩ ተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያገኙና አገራቸው የተሻለ ሠላም እንዲኖራት ከማድረጉ በላይ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሠላሟ እንድትመለስ የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በጋና እና ሊቢያ የሩጫ ውድድሮችን ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ