አርዕስተ ዜና

የአዲስ አበባ የብስክሌት ክለቦች ሻምፒዮና ተጠናቀቀ

19 Mar 2017
538 times

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2009 በአዲስ አበባ የብስክሌት ክለቦች ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አሸናፊ ሆኑ።

በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌደሬሽን የተዘጋጀው ሻምፒዮና ዛሬ ሲጠቃለል 40 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ውድድር በስታዲየም አካባቢ ተካሂዷል።

በዚሁ የአጠቃላይ ውጤት የወንድ ኮርስ ውድድር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና በማውንቴን ውድድር የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ለአንድ ዓመት ያህል በሁለቱም ፆታ በማውንቴንና በኮርስ የብስክሌት ውድድር ታዳጊዎችን ጨምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች  ተካሂደዋል።

በዚህ ሻምፒዮና የቡድን  ወንዶች ማውንቴን ውድድር የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።

የካ ክፍለ ከተማና ጋራድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስፖርት ክለብ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችለዋል።

በተመሳሳይ በቡድን የወንድ ኮርስ ውድድር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አሸናፊ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የአፍሪካ ስደተኞች ስፖርት ክለቦች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ረዘነ በየነ እንደገለጹት፤ አምስት ክለቦችን ያሳተፈው የአዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና የብስክሌት ውድድር ዋና ዓላማው ታዳጊዎችን ማፍራት ነው።

የብስክሌት ስፖርትንም ለማስፋፋት ውድድሮችን የማብዛት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለአንድ ዓመት ያህል ሲካሄድ የቆየው ይኽው ውድድር ታዳጊ ወጣቶችን ጨምሮ  አምስት ክለቦች የተሳተፉበት ከ16 ጊዜ በላይ ውድድሮች መካሄዳቸው ተውቋል።

በግልና በቡድን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ተሳታፊዎችም የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ