አርዕስተ ዜና

ማዕከሉ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለሌላ አገልግሎት እየዋለ መሆኑን ተገልጋዮች ተናገሩ

18 Mar 2017
437 times

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 የጃንሜዳ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለሌላ አገልግሎት እየዋለ ነው ሲሉ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን ገለጹ።

ማዕከሉ በበኩሉ የማዘውተሪያ ስፍራው ውስጥ የግንባታ ተቋራጮች ዕቃ ማስቀመጣቸውንና ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው አትሌቶችና የማዘውተሪያ ስፍራው ተገልጋዮች ማዕከሉ ከሚሰጠው አገልግሎት በተለየ መልኩ የሚከናወኑ ግንባታዎች ህልውናውን እንዳያጠፉት ስጋት አድሮብናል ብለዋል።

ስፍራው የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በተለይም የፈረስ ጉግስ፣ ትግል፣ የገና ጨዋታና የመሳሰሉትን ባህላዊ ስፖርቶች በማስተናገድ ይታወቃል፡፡

የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሩጫን ጨምሮ እግር ኳስና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮችም የሚከናወኑበት ነው።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሜዳውን የወደፊት የስፖርት ማዕከልነት ሥጋት ላይ የሚጥሉ ክስተቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን አትሌቶችና የማዕከሉ ተጠቃሚዎች እየገለጹ ነው።

በቤትና በሕንፃ ግንባታዎች ምክንያት የሜዳው ስፋትና ወርድ እየጠበበ መምጣቱን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የታዘቡት።

ግንፍሌ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እግር ኳስ ለመጫወት በተደጋጋሚ ወደ ጃንሜዳ እንደሚመጣ የተናገረው ወጣት ኑረዲን ሙሴራ ሁኔታው እንደሚያሳስበው ገልጿል።

ወጣት አቡበከር አወል በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች በግንባታ ምክንያት መጥፋታቸውን ያስታውሳል።

በዚህ ምክንያት ወጣቶች ጊዜ የሚያሳልፉበት ቦታ በማጣት ለተለያዩ ሱሶች መጋለጣቸውን ነው ተናግሯል።

ጃንሜዳም “በግንባታ ምክንያት ከሚጠፉ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች አንዱ እንዳይሆን የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል” ብሏል።

አትሌት የማነ ጸጋዬ በበኩሉ የአትሌቶች የልምምድ ቦታና የማዘውተሪያ እጦት ፈተና በሆነበት ወቅት ጃንሜዳን በእንክብካቤ በመያዝ ለስፖርተኞች ማመቻቸት ይገባል ነው ያለው።

ግዙፉ የጃንሜዳ ሁለገብ የስፖርት ሜዳ መቆራረጥና ስፋቱ እየቀነሰ መምጣት እንደሚያሳስበው የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህን ነው።

ቀደም ሲል በመዲናዋ የሚገኙ በርካታ አትሌቶችና ስፖርተኞች ልምምድ የሚሰሩበት ማዘውተሪያ ስፍራ እንደነበር በማስታወስ።

በአሁኑ ወቅት ብቸኛውና በርካታ ስፖርተኞችን የሚያስተናግደው ጃንሜዳን “ለአትሌቶች ልምምድ መስሪያ በማመቻቸት ማህበሩ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሰራ ነው” ብሏል።

በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የጃንሜዳ የትምህርትና ስልጠና ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ በርሄ እንዳሉት በመንገድና በህንፃ ግንባታ የተሰማሩ ሁለት የግንባታ ተቋራጮች ያለአግባብ በማዕከሉ ውስጥ የግንባታ ቁሳቁሶች በማስቀመጣቸው በሜዳው ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው።

''እየተገነባ ከሚገኘው ዘመናዊ ጂምናዝየም ውጪ ሌላ ግንባታ እየተካሄደ እንዳልሆነና በማዕከሉ ተቋራጮች የግንባታ ቁሳቁሶችና መኪኖችን ለማስቀመጥ እንዲሁም ሲሚንቶ ለማገናኘት በጊዜያዊነት እንዲጠቀሙበት ተፈቅዶላቸው ነበር'' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ጠቁመው፤ እስኪወጡ ድረስ የተወሰነ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ብለዋል።

እነዚህና መሰል ስራዎች ከአካባቢው እንደሚነሱና የማዘውተሪያ ስፍራውን ለስፖርተኞች ምቹና ሜዳውን አረንጓዴ ለማድረግ በእቅድ መያዙን ተናግረዋል።  

ጃንሜዳ ለአትሌቶቹና ለስፖርተኞ ምቹ እንዲሆን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም  ተናግረዋል።

ሜዳውን በማስተካከልና በማደስ በጨረታ ላይ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ ስራው እንደሚጀመር ገልፀዋል።

በመዲናዋ ውስን የማዘውተሪያ ስፍራዎች ቢኖሩም ያሉትን የመንከባከብና የማደስ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣት ማዕከላት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ ብርሃኑ ባዩ ናቸው።

ማህበረሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በስፖርት ተጠቃሚ ለማድረግ ለማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ የሚውል ከ247 ሚሊዮን ብር  በላይ መመደቡን ገልፀዋል።

የጃንሜዳ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ከ723 ሺህ በላይ ካሬ ሜትር ስፋት የሚሸፍንና የራሱ የሆነ ካርታና ፕላን ያለው የማዘውተሪያ ስፍራ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ