አርዕስተ ዜና

ለአርባ ምንጭ ከነማ እግር ኳስ ክለብን ማጠናከሪያ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተፈቀደ

690 times

አርባ ምንጭ መጋቢት 4/2010 የአርባምንጭ ከነማ እግር ኳስ ክለብን ለማጠናከር ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተፈቀደ።

ለክለብ ውጤት ማነስ ምክንያት በሆኑ የቴክኒክና አደረጃጀት ችግሮችን ለመፍታት የክለቡ ቦርድ አባላት ተቀናጅተው እንዲሰሩም የክለቡ ጠቅላላ ጉባኤ አሳስቧል።

ጠቅላላ ጉባኤው ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢና የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት በመጀመሪያው ዙሪ ፕሪሚየርሊግ በክለቡ ውስጥ በተፈጠረ አደረጃጀት፣ በቴክኒክና በጥቅም ግጭት ምክንያት የሚጠበቀው ውጤት አልተመዘገበም፡፡

በክለቡ ደጋፊዎች በኩል የጎላ ስፖርትዊ ጨዋነት ችግር ባይኖርም በአንዳንድ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነት አመራሮችና አሰልጣኞችን የመከፋፈልና ተጫዋቾችን የማሸማቀቅ ዝንባሌዎች ተስተውለዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት ከቦርድ አባላት ጀምሮ አሰልጣኞችን፣ የቴክኒክ አመራሮችና የቡድን መሪዎች ቢቀየሩም ውጤቱ ላይ የጎላ ለውጥ አለመምጣቱን ከንቲባው ገልጸዋል።

ክለቡ በቂ የሆነ በረኛ፣ ተከላካይና አማካይ ተጫዋቾች ቢኖሩትም በአጥቂው በኩል ባለው ክፍተት ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን ነው ያስረዱት።

ጉባኤው በፕሪሜየርሊጉ 2ኛው ዙር ክለቡን ለማጠናከር ከዞን፣ ከከተማ አስተዳደሮችና ከወረዳ ድጋፍ የሚደረግ 18 ሚሊዮን ብር በጀት በሙሉ ድምጽ ማጽደቁንም ከንቲባው አመልክተዋል።

የክለቡ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታዬ ሰይፉ በበኩላቸው  ክለቡ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የተጫዋቾችን የቴክኒክና ስፖርታዊ ብቃት ችግሮች በአግባቡ መፍታት ሲችል ነው።

"በአሰልጣኞች፣ ተጫዋቾችና በቴክኒክ ኮሚቴ መካከል ያለው አላስፈላጊ ግንኙነትና ሹክቻ እንዲሁም በአንዳንድ ተጫዋቾች ላይ የሚታይ የስነ ምግባር ጉድለት ሊታረም ይገባል" ብለዋል፡፡

ክለቡ የሚወክለውን ህዝብ ባህሪ እንዲላበስ በአመራሩ በኩል የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የክለቡ የበላይ ጠባቂና የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ ናቸው፡፡

ክለቡን ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ የሚሰራው ሥራ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ገልጸው፣ የክለቡን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ህዝቡን ያሳተፈ ሥራ መሰራት እንዳለበት አስገንዘበዋል።

"የክለቡ አመራሮች አሁን በክለቡ ውስጥ የተስተዋለውን የቴክኒክ፣ የአደረጃጀትና የተጫዋቾች የቅንጅት ችግሮችን በመፍታት ቡድኑን ከውጤት ቀውስ ማውጣት ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን