አርዕስተ ዜና

የዳኞች ውሳኔና የውድድር መቆራረጥ ችግሮች ሊታረሙ ይገባል ተባለ

604 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙር የታዩ የዳኛ ውሳኔና የውድድር መቆራረጥ ችግሮች በሁለተኛው ዙር እንዲታረሙ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ጠየቁ  ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና 16ቱ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች የአንደኛ ዙር ውድድር አፈጻጸምን አስመልክቶ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

ዳኞች በጨዋታ ላይ የሚሰሯቸው ስህተቶች በቡድኖች ውጤት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙር ከታዩ መሰረታዊ ችግሮች መካከል መሆኑን የወላይታ ድቻ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ወሲሶ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች ይልቅ በክልሎች በሚደረጉ ጨዋታዎች የዳኞች ስህተት ጎልቶ እንደሚታይ የጠቀሱት አቶ አሰፋ በሁለተኛው ዙር መታረም እንዳለበት ተናግረዋል።

የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በመጀመሪያው ዙር ውድድሮች በተደጋጋሚ መቆራረጥ በስፋት መስተዋሉ በክለቦች ውጤት እንዲሁም በተጫዋቾች የስነልቦና፣ የአካልና የአዕምሮ ዝግጅት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

ክለቦችን ተገቢ ላልሆነ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑም እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሊጉን ውድድር ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት ማጠናቀቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስረድተዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ተቀራራቢ በመሆኑ በሁለተኛው ዙር የዳኞች አመዳደብ ላይ ጥንቃቄ ይፈልጋል ብለዋል አስልጣኝ ውበቱ አባተ።

የዳኝነት ውሳኔ ቅጽበታዊ በመሆኑ ስህተት ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር የገለጹት ክለቦች በዳኝነት ምደባ ላይ ፍትሃዊነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

ኮሚሽነሮች ስለ ጨዋታ የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች አጠቃላይ በጨዋታ ላይ ያሉ ሁነቶችን ሙሉ ምስል የሚያሳዩ አይደሉም ሲሉም ክለቦች ጨምረው አስታውቀዋል።

በውይይቱ ጨዋታዎች ሲራዘሙ መረጃው በቶሎ አለመድረስና አንዳንድ ሜዳዎች ለጨዋታ አስቸጋሪ መሆናቸውም ክለቦቹ ያነሷቸው ችግሮች ናቸው።

የብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ አባል አቶ ሸረፋ ዲሊቾ በዳኞች ውሳኔ ክለቦች መጎዳታቸውንና በውጤት ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩ ዳኞች መቀጣታቸውን ተናግረዋል።

የዳኝነት ምደባ በክለቦች ፍላጎት የሚከናወን ሳይሆን የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ስራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሸረፋ ተደጋጋሚ የዳኞች ምደባን ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለውድድሩ መንፈስ ማማር የዳኞች ድርሻ ከፍ ያለ ቢሆንም ሁሉም የድርሻውን መወጣት ከቻለ የሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም አክለዋል።

ዳኞች በእግር ኳስ ህጎች አተረጓጎም ላይ ያሉባቸውን ስህተቶች በመለየት የክህሎት ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ውድድሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ በበኩላቸው በመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብሮች መቆራረጥ እንደ ክፍተት መታየቱን አንስተዋል።

አንዳንድ ጨዋታዎች ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች መራዘማቸውንና በተቻለ ፍጥነት ተስተካካይ ጨዋታ እንዲያካሂዱ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ ጊዜ ጨዋታዎች ሲራዘሙ ለክለቦች በቶሎ የማሳወቅ ችግር እንዳለ ያመኑት አቶ አበበ ይህም የሚታረም መሆኑን ተናግረዋል።

'በሜዳዎች ጥራት ላይ አወዳዳሪውና ተወዳዳሪው ተቀራርቦ መስራት አለበት እኛ የሜዳዎችን ጥራት ተከታትለን ባላሟሉት ላይ ሜዳዎችን እስከማገድ እርምጃ የሚደርስ ርምጃ እንወስዳለን' ነው ያሉት።

የሁለተኛው ዙር ውድድር የተሻለ እንዲሆን ክለቦችና ፌዴሬሽኖች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በተያያዘ ዜና በግምገማው ላይ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ውድድር የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተካሂዷል። ዕጣው የወጣው ክለቦቹ ዙሩን ባጠናቀቁበት ደረጃ መሰረት ነው።

16ቱ ክለቦች ከ1-16 የዕጣ ቁጥር የተሰጣቸውና በዛ መሰረት የሚጫወቱ ሲሆን አንድ ክለብ የዕጣ ቁጥሩ ከሌላኛው ተጋጣሚ የሚያንስ ከሆነ በሜዳው ይጫወት በሚለው ሀሳብ ክለቦች በመስማማታቸው ድልድሉ ወጥቷል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ቡና ከወልዲያ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ ከተማ፣ ፋሲል ከተማ ከአዳማ ከተማና መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ ይገናኛሉ።

ጅማ አባጅፋር ከደደቢት፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከመቀሌ ከተማ፣ ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

ጨዋታቸውን ያሸነፉ ቡድኖች በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉ ሲሆን በአጠቃላይ የግማሽ ፍጻሜና የፍጻሜ ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ሜዳዎች በዕጣ ይወሰናሉ።

ፌዴሬሽኑ ውድድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ቀናት በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን