አርዕስተ ዜና

ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴና ኃይሌ ገብረስላሴ ለአሸናፊ አትሌቶች የገንዝብ ሽልማት አዘጋጅተዋል

527 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴና ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ አገራቸውን ወክለው ሜዳሊያ ለሚያመጡ አትሌቶች የገንዝብ ሽልማት እንደሚሰጡ ቃል ገቡ።

በስፔን ቫሌንሺያ በሚካሄደው 23ኛው ዓለም አቀፍ ግማሽ ማራቶንና በአልጀሪያ 5ኛው አህጉር አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶች ትናንት ምሽት በአራራት ሆቴል ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤትና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ በላይነህ ክንዴ በ23ኛው ግማሽ ማራቶንና በ5ኛው አህጉር አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ወርቅ ለሚያመጡ አትሌቶች 10 ሺህ ብር እንደሚሸልሙ ተናግረዋል።

የብርና የነሀስ ሜዳሊያ ለሚያገኙ አትሌቶች ደግሞ የ7 እና የ5 ሺህ ብር ሽልማት አበረክታለሁ ብለዋል ተናግረዋል።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴም ጥሩ ውጤት ለሚያመጡ አትሌቶች ከአቶ በላይነሀ ክንዴ ቃል የተገባውን ያህል የገንዘብ ሽልማት እንደሚያበረክት ገልጿል።

ሻለቃ ኃይሌ ለአትሌቶች ባስተላለፈው መልዕክት "የበፊቶቹ ታላላቆቻችሁ የሰሯቸውን ታሪኮች መስራት ትችላላችሁ" ሲል አበረታቷቸዋል።

ከምንም በላይ አትሌቶች መልካም ስነ ምግባርና ስፖርታዊ ጨዋነት መላበስ እንዳለባቸውም አሳስቧል።

በሁለቱም ውድድሮች የሚካፈሉ አትሌቶችና አሰልጣኞች ለውድድሩ ጥሩ ዝግጅት እንዳደረጉና ለአገራቸው ጥሩ ውጤት ይዘው እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም በስፔን ቫሌንሺያ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን በሁለቱም ጾታ በ10 አትሌቶች ትሳተፋለች።

በአህጉር አቀፉ አገር አቋራጭ ውድድር ደግሞ መጋቢት 8 ቀን 2010 ዓ.ም በ28 አትሌቶች ተሳታፊ ትሆናለች።

በአልጄሪያው ውድድር በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንድና ሴት፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትርና ሁለቱንም ጾታ ያካተተ የዱላ ቅብብል /ድብልቅ ሪሌ / የምትካፈል ይሆናል።

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን