አርዕስተ ዜና

ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ነገ በሆሳዕና ከተማ ይጀመራል

606 times

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2010 ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ነገ በሐዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ይጀመራል።

ከመጋቢት 4 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር 10 የቦክስ ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ የቦክስ ፌደሬሽን በዘንድሮው ዓመት ከሚያካሂዳቸው የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድሮች ሁለተኛው ነው።

በፌደሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር እንዲሁም ከደቡብ ክልል የተውጣጡ ናቸው።

ክለቦቹ 12 የወንዶችና ስድስት የሴቶች ተወዳዳሪዎችን ይዘው እንደሚቀርቡ የተናገሩት አቶ ስንታየው ተወዳዳሪ ክለቦች ከሁሉም ክልሎች ያልተገኙት የቦክስ ክለብ የሌላቸው በመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በውድድሩ ላይ በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም ግጥሚያ የሚካሄድ ሲሆን፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ባሉ ክብደቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ይህንን ውድድር እንደሌሎቹ ስፖርቶች በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ለማካሄድ ይህንን ውድድር እንደመነሻ ለመጠቀም መታቀዱን አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።

ውድድሩ ሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው የአፍሪካ የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ቦክሰኞችን ለመምረጥና ለመመልመል እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

በውድድሩ በየክብደቱ ምርጥ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሚረዳ አስረድተዋል።

የዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድር በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም እንደተካሄደ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የቦክስ ፌደሬሽን ቀጣዮቹን ሁለት የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ሻምፒዮና በሚያዝያና ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ላይ እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት ለወታደሮች ይሰጥ ነበር።

በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርቱ መለመድና መስፋፋት ጀመረ።

የክለቦች ምስረታም በዛው ወቅት የተጀመረ ሲሆን፤ በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን