አርዕስተ ዜና

የስፖርት ቤተሰቡ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

503 times

ባህር ዳር መጋቢት 3/2010 መላው የስፖርት ቤተሰብ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ።

ከአምስት ሺህ 700 በላይ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት 6ኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ጨዋታ በባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን ተጀምሯል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ወለላ መብራቱ ውድድሩ ሲጀመር እንተናገሩት የክልሉ መንግስት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውና ትናንት የተጀመረው 6ኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ጨዋታ ለክልሉና ለሀገሪቱ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የጎላ ድርሻ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በህዝቦች መካከል ሰላምን፣ አንድነትን፣ ወዳጅነትን፣ መከባበርና መደጋገፍን ለማጠናከር ስፖርት የጎላ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝም ወይዘሮ ወለላ አስረድተዋል።

" ስፖርት የጾታ፣ የብሔርና መሰል አስተሳሰቦችን የማያስተናግድ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠ ተግባር በስፖርት ማዘውተሪያዎች እየተስተዋለ ይገኛል" ብለዋል።

ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስም ተሳታፊ ስፖርተኞች፣ ባለሙያዎች፣ ደጋፊዎችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማወክ የሚንቃሳቀሱ ኃይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።  

ስድስተኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ጨዋታን በተጋባዥነት ተገኝታ የከፈተችው ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ስፖርት በህዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልጻለች።። 

ተሳታፊ ስፖርተኞችም በሚያደርጉት ውድድር ማሸነፍንም ሆነ መሸነፍን በፀጋ በመቀበል እርስ በእርስ ስፖርትዊ ጨዋነትና ልምዶችን መለዋወጥ እንደሚገባቸው አስረድታለች።

ከስፖርታዊ ውድድሩ ጎን ለጎንም የመጣችሁበትን አካባቢ ወግና ባህል ከማስተዋወቅና ከማሳደግ ባለፈ ይበልጥ አንድነታችሁን ልታጠናክሩ ይገባል ሲሉም መክረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ክብረት መሀሙድ በበኩላቸው በአስተዳደሩ ጥረትና የክልሉ መንግስት በሚያደርገው ድጋፍ ከተማዋን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የቱሪዝም ፍሰቱ እያደገ እንዲሄድ ከማድረጉ በላይ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል። 

"በሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች የስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያደፈርሱ አመለካከቶች እየታዩ በመሆኑ የከተማዋ ሕዝብ ሊከላከላቸው ይገባል" ብለዋል።

በስድስተኛው የመላው አማራ ጨዋታ ለመሳተፍ ወደከተማው የመጡ የስፖርት ልዑካን ተሳታፊዎች በቆይታቸው የኦሎምፒክ ስፖርት መርህን በመላበስ አንድነትና ፍቅርን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውድድሩ መክፈቻ ላይ የተገናኙት የባህር ዳርና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እግር ኳስ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታም የአዊ እግር ኳስ ክለብ 5 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ከትናንት ጀምሮ እስከ መጋቢት 16 በሚካሄደው የመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድርም እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ 18 ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ታውቋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን