አርዕስተ ዜና

ቡድኑ በታዳጊ ወጣቶች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስታወቀ

17 Feb 2017
467 times

ጅማ የካቲት 10/2009 የጅማ አባቡና እግር ኳስ ቡድን ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በታዳጊ ወጣቶች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስታወቀ።

ቡድኑ ከጅማ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የታዳጊ እግር ኳስ የአሰልጣኞች ስልጠና በጅማ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የቡድኑ ፕሬዚዳንት አቶ አበዱልከሪም አባገሮ በእዚሁ ወቅት እንዳሉት ቡድኑ ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በየደረጃው ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ አቅዶ እየሰራ ነው።

ይህንን ለማሳካት ከጅማ ዞን 21 ወረዳዎችና ከጅማ ከተማ ለተውጣጡ 49 ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የስልጠናው ተሳታፊዎች ለ12 ቀናት የሚሰጠውን ስልጠና አጠናቀው ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ ታዳጊ ወጣቶችን በመመልመልና በማሰልጠን ለክለቡ ተተኪ እግር ኳስ ተጨዋቾችን ለማፍራት ይሰራሉ" ብለዋል።

ለጅማ አባቡና " ቢ" ቡድን ተጨዋቾችን መልምለው እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት።

የጅማ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጆቢር በበኩላቸው "ስልጠናው የጅማ አባቡና ስፖርት ቡድንን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝና አምራች ዜጋን የማፍራት አገራዊ ግብን ለማሳካት ያስችላል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ የእግር ኳስ ክለቦች ተጫዋቾችን ከውጭ አገር በከፍተኛ ወጪ ለማስፈረም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አዋጪ ባለመሆኑ በአገር ውስጥ ተተኪ ተጫዋቾችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች የሚገኙት በስልጠናና በውድድር በመሆኑ የጅማ አባቡና የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ