አርዕስተ ዜና

በፕሪሚዬር ሊጉ ዳኞችና ኮሚሽነሮች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ ተገመገመ

16 Feb 2017
424 times

አዲስ አበባ የካቲት 9/2009 በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ አንደኛ ዙር የእግር ኳስ ውድድር የዳኝነት ስህተት የበዛበትና ኮሚሽነሮችም ሥራቸውን በአግባቡ ያልተወጡበት እንደሆነ ተገመገመ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ 2009 ዓ.ም አንደኛ ዙር የወንዶች ፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ሂደቱን በወላይታ ሶዶ ከተማ ገምግሟል።

በግምገማው ኮሚሽነሮች ጨዋታውን በንቃት ተከታትሎ ሚዛናዊ የሆነ ሪፖርት ለፌዴሬሽኑ ሲያቀርቡ እንዳልነበር ነው ክለቦች ቅሬታቸውን ያሰሙት።

ኮሚሽነሮች በእግር ኳስ ውድድር የጨዋታውን ሂደት በመከታተል በዳኞች ሆነ በተጫዋቾች ወይም በስታዲየሙ የነበሩ ክስተቶችን ተከታተለው የነበረውን ሂደት ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

እንዲያም ሆኖ በፕሪሚዬር ሊጉ የሚመደቡ ኮሚሽነሮች ጨዋታውን ተከተታሎ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሪፖርት በማድረግ ረገድ ውስንነቶች እንደተስተዋለባቸው ነው ክለቦች የሚናገሩት።

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ እርቁ እንደሚሉት ፌዴሬሽኑን ወክለው የሚመጡ አንዳንድ ኮሚሽነሮች ለውድድሩ በቂ ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋሉም።

''አንዳንዶቹም የዳኞችን ስህተት በትክክል ሪፖርት ከማድረግ ይልቅ ለዳኞች ከለላና ዘብ ሆነው ነው የሚሰሩት'' ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የወላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ  ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሊሶ "የኮሚሽነሮች ጉዳይ ግልፀኝነት የጎደለውና ወገንተኝንት የሚታይበት በመሆኑ ሊስተካከል ይገባዋል" ብለዋል።

"ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ በመሆናቸው በፌዴሬሽኑ ሌሎች አማራጭ ቦታዎች ላይ ቢሰሩ የተሻለ ይሆናል እንጂ በኮሚሽነርነት ደረጃ ስራቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም" ነው ያሉት።

የበዙት በፕሪሚዬር ሊጉ ተካፋይ የሆኑ ክለቦችም በዳኞችና ኮሚሽነሮች የአየፈፃጸም ክፍተት መኖሩን ነው በግምገማው ያነሱት።

በግምገማው ክለቦች ካነሷቸው ቅሬታዎች የዳኝነት ውሳኔዎች ገዝፈው የታዩ ችግሮች እንደነበሩ የሚያንጸባርቁ ናቸው።

በፕሪሚዬር ሊጉ የክለቦች የደረጃ ሰንጠረዥ የተቃራረበና ብዙም የነጥብ ልዩነት የሌላቸው በመሆኑ በቀጣይ አሸነፊ ለመሆንና ከወራጅ ቀጣና ለመውጣትም የሚደረገው ትንቅንቅ ከፍተኛ እንደሆነ ይጠበቃል።

ስለዚህ በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የተሻለ ዳኝነት መኖር እንዳለበት ነው ክለቦቹ አጽንኦት ሰጥተው ያነሱት።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በአንደኛው ዙር የዳኝነት ስህተቶች እንደነበሩና በኮሚሽነሮች በኩልም ችግሮች እንደነበሩ አምኖ በቀጣዩ ዙር ማስተካከያ እንደሚደረግ አስታውቋል።

በፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ አባል አቶ ሸረፋ ዳሊቾ ኮሚሽነሮች የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በትክክል ሪፖርት የማድረግ ችግር እንደሚታይባቸው ገልጸዋል።

''በኛ በኩልም ኮሚሽነሮች የጨዋታውን ሂደት በትክከል ሪፖርት ባለማድረጋቸው የተቸገርንበት ጉዳይ ነው'' ብለዋል።

በዳኞች በኩልም በአንደኛው ዙር ስህተቶች እንደነበሩ ገልጸው፤ይህን ተከትሎም እስከ ስድስት ወር ድረስ ውድድሮችን እንዳይዳኙ ቅጣት የተጣለባቸው እንዳሉም በማሳያነት አንስተዋል።

በቀጣይም የተሻለ ዳኝነት እንዲኖር በክለቦች በኩልም ለዳኞቻች ጥበቃና ከለላ በመስጠት በነፃነት እንዲዳኙ ማድረግ እንጂ ተጽዕኖ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በአንደኛው ዙር በድክመት ከተነሱ ጉዳዮች በተቃራኒ በጠንካራ ጎን ከተነሱ ሀሳቦች መካከል የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የተሻለ ነገር የታየበት እንደነበር ተገልጿል።

እንዲሁም በ 2009 ዓ.ም አንደኛው ዙር የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚዬር ሊግ ውድድሮች ሳይቆራረጡ መካሄዳቸው ሌላው በጠንካራ ጎን የተነሳ ሆኗል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ