አርዕስተ ዜና

የግድቡ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሩጫ ውድድር ሊካሄድ ነው Featured

16 Feb 2017
1072 times

አዲስ አበባ የካቲት 9/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመላ አገሪቱ የሩጫ ውድድር ይካሄዳል።

"ጊዜ የለንም እንሮጣለን፤ ለህዳሴው ግድብ እንቆጥባለን" በሚል መሪ ቃል በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች የስድስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም ይካሄዳል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅርተ ታምር ለኢዜአ እንደገለጹት የሩጫ ውድድሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ነው።

በውድድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በመዲናዋ በሚካሄደው ውድድርም 100 ሺህ ያህል ዜጎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

ለውድድሩ የተዘጋጀው የመወዳደሪያ መለያ ህትመት መጠናቀቁን ገልጸው ከመለያው ሽያጭም እስከ 30 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የጠቆሙት።

ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች ለውድድሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎችም የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን በውድድሩ ለግድቡ ግንባታ የሚውል የቦንድ ሽያጭ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

የግድቡ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ከሩጫው በተጨማሪ የእግር ኳስና የብስክሌት ውድድሮች እንደሚካሄዱም ጠቅሰዋል።

የሩጫ ውድድሩ ኅብረተሰቡ ለህዳሴው ግድብ ያለውን የጋራ መግባባት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ አገራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ስድስተኛ ዓመት የማጠቃለያ በዓል መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ይከበራል።

በተያዘው ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከተለያዩ ምንጮች 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ይጠቁማል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ