አርዕስተ ዜና

ወጣት አትሌቶች ከመም ውድድሮች ይልቅ ወደ ማራቶን እያዘነበሉ ነው

16 Feb 2017
835 times

አዲስ አበባ የካቲት 9/2009 የመም ውድድሮች መቀነስና የልምምድ ቦታ እጥረት ወጣት አትሌቶች ወደ ማራቶን ውድድሮች እንዲያዘነብሉ ማድረጉን ታዋቂ አትሌቶች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ በመም (ትራክ) የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጿል።   

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውድድሮች በምትታወቅባቸው በ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር ውድድሮች የበላይነት ይዛ ቆይታለች።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በነዚህ ርቀቶች በኬንያና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ተወዳዳሪዎች አትሌቶች እየተቀደሙ፤ የበላይነቱ እየተቀዛቀዘ መጥቷል።

ለዚህ ምክንያቱ ወጣት ተተኪ አትሌቶች ወደ ረጃጅም ርቀት አንጋፋዎቹ ደግሞ ወደ ማራቶን ውድድሮች የመተካካት ሂደቱ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ይስተዋላል።

ወጣት አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ወደ ማራቶን ማዘንበል አገሪቷ የበላይነቷን አስጠብቃ በቆየችባቸው ርቀቶች ተተኪዎች እንድታጣ ማድረጉ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ነው አስተያየት ሰጪዎች የተናገሩት።

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡት ታዋቂ አትሌቶች እንደገለጹት፤ የመም ውድድሮች መቀነስና  የልምምድ ስፍራዎች ምቹ አለመሆን አትሌቶች ወደ ማራቶን እንዲገቡ ማድረጉ በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

የአትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንትና በሁለት የኦሎምፒክ ውድድሮች በ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያዎችን ያጠለቀው አትሌት ስለሽ ስህን እንደተናገረው፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም አገሮች የጎዳና የማራቶን ውድድሮች እየበዙ ነው።

በተለይ የትራክ ውድድሮች እየተቀዛቀዙና እየጠፉ በመምጣት ላይ መሆናቸውን አመልክቶ፤ ወጣት አትሌቶች የተሻለ ጥቅምና ክፍያ ያለው የማራቶን ውድድሮች እየመረጡ መሆኑንም ነው የተናገረው።

አትሌቶች የመም ላይ ልምምድ ማድረጊያ ስፍራም ያለመኖር ችግር መሆኑን የጠቆመው አትሌቱ፤ ይህንኑ ለማቃለል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የገለጸው።

ማህበሩ ከኢፌዴሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በተለይ እየጠፋ ያለውን የአትሌቶችን የልምምድ መስሪያም ለመፍታት ጥረት እያደረግን  መሆኑን ጠቁሟል።

አትሌት የማነ ጸጋዬ በበኩሉ ''በተለይ የ10ና የ5ሺ ውድድሮች ከኦሎምፒክ ውድድሮች ይውጣል መባሉ፣የውድድሮችም መቀነስና የመም መሮጫ ማዘውተሪያ ቦታ እጦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣት በዚሁ ርቀት ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች መቀዛቀዝ ምክንያት ነው'' ብሏል።

የአትሌቶች ማኔጀሮችም ጥቅም ወደሚገኝባቸውና በብዛት በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ እያደረጉም መሆኑን ይጠቁማል።

''ችግሩ በዓለም ላይ ያሉ ውድድሮች ከአጭር ጀምሮ እስከ ረጅም ርቀቶች ትኩረት እየተሰጠው አይደለም'' የምትለው ደግሞ የረጅም ርቀት ሯጯ አትሌት ገለቴ ቡርቃ ናት።

ቀደም ሲል የ5ሺና የ10ሺ ሜትር ላይ ስትካፈል የቆየችው ገለቴ፤ በቀጣይ በማራቶን ውድድር ለመካፈል እየተዘጋጀች መሆኑን ተናግራለች። እርሷ በነበረችበት የውድድር ዓይነት ተተኪዎች እንዲኖሩ ትፈልጋለች። 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚያብሔር ገብረማርያም  ወጣት አትሌቶች የመም ውድድሮች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ያምናል።

የመም ውድድሮች የመካከለኛና የረጅም ርቀት ሯጮች ላይ የአትሌቶችን ተሳትፎ ትኩርት በመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

''በአጭር ርቀት ላይ ከሰራን ለመካከለኛና ለረጅም ርቀት ተተኪዎችን ለማፍራት በክለቦችና በብሔራዊ ቡድኑ ላይ በትኩርት መስራት አለብን'' ብሏል።

በአሁኑ ወቅት የረጅም ርቀት ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች በቀጣይ በማራቶን የሚወዳደሩ መሆኑን ጠቁሞ፤ በረጅም ርቀት ተወዳዳሪ ለማግኘት ችግር ሊገጥም እንደሚችል ነው ገብረእግዚያብሔር የተናገረው።   

ኢትዮጵያ እኤአ ከ1956 ጀምሮ በተካፈለችባቸው የኦሎምፒክ ውድድሮች 22 የወርቅ 10 የብርና 21 የነሐስ ሜዳልያ ማግኘቷ ይታወቃል።

ከነዚህ መካከል 5 የወርቅ፣ አንድ የብርና  ሦስት የነሐስ ሜዳሊያ የተገኘው በማራቶን ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ በ5ሺና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች የተገኙ ናቸው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ