አርዕስተ ዜና

በዞኑ እየተዳከመ የመጣውን የስፖርት ውድድሮች ውጤት ለማሻሻል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ

16 Feb 2017
449 times

ደሴ የካቲት 8/2009 በደቡብ ወሎ ዞን እየተዳከመ የመጣውን የስፖርታዊ ውድድሮች ውጤት ለማሻሻል   ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡

የዞኑ ስፖርት ምክር ቤት  ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በተካሄደበት ወቅት የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እጅጉ መላኬ እንደገለጹት ዞኑ በስፖርታዊ ውድድሮች የሚያስመዘግበው ውጤት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡

አካባቢው ከቀድሞ ታሪኩ አንጻር እየተመዘገበ ያለው ውጤት የስፖርት አፍቃሪውን ስሜት እየጎዳ መሆኑን ከህብረተሰቡ የሚመጣው አስተያየት ያረጋግጣል።

"በዘርፉ የታጣው ውጤት ዋና ምክንያትም የበላይ አመራሩ ትኩረት ማነስ፣ ፌደሬሽኖች በቁርጠኝነት አለመስራትና የህዝቡ ተሳትፎ መቀነስ ናቸው "ብለዋል።

ችግሩን  በመፍታት ዞኑ ይታወቅባቸው የነበሩትን የስፖርት ዓይነቶች ወደ ውጤት በማምጣት ወደ ቀድሞ ደረጃቸው ለመመለስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው፡፡

በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ መምሪያ የስልጠናና የውድድር ስፖርቶች ባለሙያ አቶ ጸጋዬ ለገሰ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርቱ መሰረት ዞኑ በአምስተኛው የመላ አማራ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ በኦሎምፒክ ስፖርቶች ከተወዳዳሪ ዞኖች 9ኛ ወጥቷል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደ ተመሳሳይ  ውድድር  የነበረው ደረጃ ሁለተኛ ነበር።

በተለይ ከማህበረሰቡ የሚሰባሰበው የስፖርት ገቢ አነስተኛ መሆንና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች አለመስፋፋት ውጤታማ ስፖርተኞችን ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡

ምክር ቤቱ የተነሱት ችግሮች በያዝነው ዓመት እንዲፈቱ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

የ10 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በጀት ያጸደቀ ሲሆን ገንዘቡ ከተለያዩ የገቢ ምንጮችና መዋጮ የሚሰበሰብ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ 

ጉባኤው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ መካሄዱ በዓመቱ ለመፈጸም በታቀዱ ስራዎች ስኬታማነት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው ላይ በስፖርቱ እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ወረዳዎች፣ ተቋማትና ግለሰቦች  ዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

 

 

ኮምቦልቻ ከተማ፣ ደሴ ዙሪያና ተንታ ወረዳዎች ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ