አርዕስተ ዜና

የአርባምንጭ ከነማ እግር ኳስ ሜዳ ለጨዋታ አመቺ አለመሆኑ ተገለጸ

11 Jan 2017
1005 times

አርባ ምንጭ ጥር 3/2009 የአርባምንጭ ከነማ እግር ኳስ ሜዳ በመበላሸቱ በጨዋታ ወቅት መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተጫዋቾች ገለፁ፡፡

የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ችግሩን ለመፍታት እየሠራሁ ነው ብሏል ፡፡

ሜዳው ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ ለተለያዩ ክልላዊና ዞናዊ ሻምፒዮናዎች አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም በእንክብካቤ ጉድለት መበላሸቱን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል፡፡

የአርባምንጭ ከነማ ተጫዋች ታደለ መንገሻ እንደገለጸው በእንክብካቤ ጉድለት የሜዳው ሣር መድረቁንና መሬቱ መቦርቦሩን ተናግሯል፡፡ 

በዚህም ምክንያት በጨዋታ ወቅት እንደልብ ኳስ ይዞ ለመጫዎች እየተቸገሩ መሆኑን ገልጿል፡፡

''ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው ክፍል ብናሳውቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም'' ብሏል፡፡

''የአርባምንጭ ሜዳ ከዚህ በፊት ጥሩ ነበር አሁን ግን በጣም ተበላሽቷል ጉድጓዶችና ጠጠር በብዛት ስለሚገኝ ለመጫወት አመቺ አይደለም'' ያለው ደግሞ የደደቢቱ ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ነው ፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች በዓመት አንድ ጊዜ መጥተው የሚጫወቱበት ቢሆንም የተለያዩ ክለቦችን በሜዳው ለሚያስተናግደው የአርባምንጭ ከነማ ቡድን ከባድ እንደሚሆን ጠቅሷል፡፡

''ችግሩን ለመፍታት የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ቢያደርግ መልካም ነው'' ብሏል ፡፡

የደደቢቱ አሠልጣኝ አሥራት ሃይሌ በበኩላቸው በቅርቡ ከአርባምንጭ ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የሜዳው አመቺ አለመሆን  በውጤታቸው ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ጣሰው ጨቾ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከሦስት ዓመት በፊት በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሜዳው  ሣር እንዲለብስ ከመደረጉም በላይ ዙሪያው በግንብ መታጠሩን ገልፀዋል፡፡

አንድ ወቅት ጎርፍ ሜዳውን ሰብሮ በመግባቱና ሣሩ ውሃ የሚጠጣው ከወንዝ በጀኔሬተር ተስቦ በመሆኑ  ለሜዳው መበላሸት መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

ችግሩን ለመፍታት በአራቱም ማዕዘን የውሀ መስመር ለመዘርጋትና ሜዳውን  ለማስተካከል ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል ፡፡

የእግር ኳስ ሜዳው የአርባምንጭ ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ ከ4 ዓመት በፊት በ 6ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጥገና ተደርጐለት እንደነበር ከከተማው አግር ኳስ ክለብ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ