አርዕስተ ዜና

ብሔራዊ የወጣቶች ልማትና የለውጥ ስትራቴጂክ እቅድ ወደ ትግበራ ተሸጋገረ

356 times

አዳማ የካቲት 6/2010 የወጣቱን  ዕውቀትና አቅም ወደ ልማት ለመቀየር የሚያስችል ብሔራዊ የወጣቶች ልማትና የለውጥ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መሸጋገሩን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር ወይዘሪት እሌኒ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት ስትራቴጂክ እቅዱ ወጣቱ ያሉበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሚያስችል ነው።

በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት፣ በትምህርትና ስልጠና ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በስብዕና ልማትና ማህበራዊ ጠንቆች፣ በባህልና ስፖርት፣ በአካባቢ ጥበቃና በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ማተኮሩም ተመልክቷል፡፡

በተጓዳኝም  በሁሉም መስኮች የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በ1996 ዓ.ም የተቀረፀው የወጣቶች ፖሊስና የልማት ፓኬጅ ፍተሻና ክለሳ መካሄዱን ጠቁመዋል ።

ፓኬጁ ከዚህ ቀደም በወጣቱ ህይወት ላይ መሻሻሎች ያመጣ ቢሆንም ከተሳትፎና ተጠቃሚነት አንፃር የሚፈለገውን መሰረታዊ ለውጥ እንዳላመጣ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

"በወጣቱ ዘንድ የሚነሳውን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ዳግም ተሻሽሏል " ብለዋል ።

ወጣቱ በገጠር የሚገኝ ባዶ መሬት ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግና በከተሞች ከጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ በተጨማሪ በምግብ ዋስትና መርሀ ግብር በማቀፍ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ማድረግ የፓኬጁም ሆነ የስትራቴጂክ እቅዱ ዋና ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ እየተካሄዱ ያሉ ሀገራዊ ንቅናቄዎች በውጤት የታጀቡ መሆን እንደሚገባቸው ያመለከቱት  ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወጣቶች ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ዘነበ አካለ ናቸው።

"የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ወጣቱ ኃይል በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት፣ በባህልና ስፖርት፣ በአካባቢ ጥበቃና በጎ ፍቃድ አገልግሎት የነቃ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል" ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ማስተዋል አስማረ በሰጠችው አስተያየት ወጣቱ የሀገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ኃይል መሆኑን በመገንዘብ  ለዴሞክራሲ ማበብ መሰራት እንዳለበት ጠቁማለች።

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ የሚጠበቅበት መሆኑንም ጠቅሳለች።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ከ30 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ውስጥ ግማሽ ያክሉ ሴቶች እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን